ሰበር ዜና – የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ላይ መነጋገር ጀመረ – በገዳማዊ ሕይወት ያልተፈተኑ፣ በዲያቢሎስ ነቀፋና ወጥመድ የወደቁ፣ በፍቅረ ንዋይ እና በፍቅረ ሢመት ያበዱ፣ የውድቀት ታሪክ የሞላቸው፣ በውጭ ባሉ ሰዎች ክሥና ስሞታ እንጂ መልካም ምስክር የማይሰማባቸው፣ በአገልግሎት ያልተፈተኑ ሰዎችን መሾም አደጋው የበዛ ነው!!

 • ምልአተ ጉባኤው አስመራጭ ኮሚቴ እንደሚሠይም ይጠበቃል፤ አስመራጭ ኮሚቴው በየአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳትና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሚቀርቡ የዕጩ ኤጲስ ቆጶሳትን ጥቆማ ያሰባስባል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ፲፰ በተደነገገው መሠረት በአስመራጭ ኮሚቴው በዕጩነት ተመርጠው ከቀረቡት ቆሞሳት መካከል በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፭ ቁጥር ፺ – ፺፭ እንደታዘዘው ተሿሚ ዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በድምፅ ብልጫ ይመረጣሉ፤ ተወዳዳሪዎች ያገኙት ድምፅ እኩል ከኾነ ዕጣ የወጣለት ቆሞስ ኤጲስ ቆጶስ ኾኖ ይሾማል፡፡
 • በቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት ተቀብተው የሚሾሙት ኤጲስ ቆጶሳት የሚመደቡባቸው ዘጠኝ/ዐሥር አህጉረ ስብከት÷ ሽሬ እንዳሥላሴ፣ አክሱም፣ ዋግ ኽምራ፣ መተከል፣ ጋምቤላ፣ ወላይታ፣ ዳውሮ፣ ጉራጌ እና ጉጂ ቦረ እንደሚኾኑተጠቅሷል፡፡ በአንድ ቤተ ጉባኤ/የአብነት ትምህርት/ ምስክርነት ማግኘትና የሚሾሙበትን ሀ/ስብከት አካባቢ ቋንቋ መናገር መሠረታዊ የመምረጫ መስፈርቶች እንደኾኑ ተገልጧል፡፡

 • የኤጲስ ቆጶሳቱ ጥቆማና ምርጫ በተሻሻለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ሕግ መሠረት እንደሚከናወን ቢጠቆምም በፍትሕ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ አምስት እንደተመለከተው የምርጫው ሂደት ግልጽነት የጎደለውና በከፍተኛ ምስጢር የተያዘ መኾኑ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡

 

*      *      *

 

 • በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ አምስት መሠረት ለኤጲስ ቆጶስነት ከፍተኛ መዓርገ ክህነት የሚበቃ ቆሞስ÷ የሐዋርያነት ምልክት ያለው፣ በዚህ ዓለም ክርስቶስን ተክቶ የሚሠራ ክርስቶስን በግብር የሚመስል የክርስቶስ እንደራሴ ነው፡፡ በሥጋዊና መንፈሳዊ ተክለ ሰብእናው ነውር የሌለበት፣ ልቡናው ከሐኬት የራቀ፣ ድንግላዊ ኾኖ ሥርዐተ ምንኩስና የፈጸመ፣ በትምህርቱ ብሉይ እና ሐዲስ ኪዳናትን የተማረና የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ ሒደት በመረዳት ከፍተኛ ችሎታ ያለው፣ በጠባዕዩ የተመሰገነና ሙሉ አካል ያለው ጤናማ ሰው መኾን ይጠበቅበታል፡፡
 • ከላይ የተጠቀሰውን መስፈርት የሚያሟላ ቆሞስ ሲገኝ ኤጲስ ቆጶስነት የሚሾመው፣ በሚሾምበት ሀገረ ስብከት የሚገኙ ዕድሜያቸው ሠላሳና ከዚያ በላይ የኾናቸው ምእመናን ሲመርጡት፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሲፈቅዱ ነው፡፡
 • ማኅበረ ካህናትና ምእመናን በኤጲስ ቆጶስነት እንዲሾምላቸው ስለመረጡት አባት ደግነት፣ ትሩፋት፣ ንጽሕና እና ከነውር የራቀ ስለመኾኑ እማኝነታቸውን ወይም ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ይጠየቃሉ፡፡ ጌታችን ቅ/ጴጥሮስን ‹‹ትወደኛለኽ›› እያለ ሦስት ጊዜ መልሶ መላልሶ እንደጠየቀው፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሦስት ጊዜ እየመላለሰ ምእመናኑንና ካህናቱን ማረጋገጫ ይጠይቃቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ሕዝቡ እጃቸውን አንሥተው ‹‹የሚገባው ነው›› እያሉ ሦስት ጊዜ መልስ ይሰጣሉ፤ ያረጋግጣሉ፡፡ በዚህ መልኩ ማኅበረ ካህናቱና ሕዝበ ክርስቲያኑ እየመሰከረላቸው ይሾማሉ፡፡ ካህናቱም ሕዝቡም በሙሉ ስለ ሢመቱ ምስክር ኾነው ይቀመጣሉ፡፡
 • ክርስቶስ ‹‹እናንተን የተቀበለ እኔን ይቀበላል›› ያላቸው የቅዱሳን ሐዋርያት ተከታይና በክብራቸው የቅዱሳን ሐዋርያት አምሳያ የኾኑ ኤጲስ ቆጶሳት÷ በመዓልትም በሌሊትም ስለ ራሳቸውና ስለ ሕዝቡ ስለ ሀገሩ ስለ ዓለሙ ይጸልዩ ዘንድ ታዝዘዋል፤ ንቁሐን ትጉሃን ኾነው ኦሪትን፣ ነቢያትን፣ ወንጌልን፣ መጻሕፍተ ሊቃውንትን ምዕራፉን ቁጥሩን አንቀጹን እየለዩ ይተረጉሙና ያስተምሩ ዘንድ ይገባቸዋል፡፡ ነቢዩ ሆሴዕ ‹‹መምህሩ ደግ ከኾነ ሕዝቡም እንደርሱ ደጋግ ይኾናሉ››እንዳለው ሕዝብን በምሳሌነት በማስተማር የሚተጉ፣ ሁሉንም ጾታ ምእመናንን የሚወዱ፣ ቂም በቀል የማይዙ፣ ኀዳጌያነ በቀልና ልበ ሰፊዎች ነገር አላፊዎች መኾን አለባቸው፡፡
 • ከአጻዌ ኆኅት እስከ ቅስና ያለውን ሥልጣን ይሰጣሉ፤ እንደ ጥፋታቸው መጠን መቅጣት፣ ከሥልጣን መሻር፣ ከአገልግሎት ማሰናበትና ማገድ ይችላሉ፤ በኃጢአት የታሰረውን በሀብተ ክህነታቸው ይፈታሉ፤ ሥጋወደሙን ለምእመናን ያቀብላሉ፡፡
 • ኤጲስ ቆጶሳት በተመደቡበት ሀ/ስብከት ስማቸው ዘወትር በጸሎት ጊዜ ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ (ፓትርያርኩ) ቀጥሎ ይጠራል፡፡ ያለበቂ አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ ምክንያት ኤጲስ ቆጶሳት አንዴ ከተመደቡበት ሀገረ ስብከት አይነሡም፡፡ ኤጲስ ቆጶሳትን ያለበቂና አስገዳጅ ምክንያት ከሀገረ ስብከታቸው ማንሣት ባልን ከሚስት እንደማፋታት ይቆጠራል፡፡
 • ምእመናን በየሀገረ ስብከታቸው የሚሾሙ ኤጲስ ቆጶሳትን ሊወዷቸው፣ ሊያከብሯቸው፣ ሊታዘዙላቸው፣ በማንኛውም ሃይማኖታዊ ጉዳይ ተገቢ በኾነ መንገድ ሊደግፏቸው ይገባል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን በምእመናንና በካህናት ጉባኤ ጥቆማ በአገልግሎት ብቃታቸው ተመስክሮላቸው የሚሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት ከመንበር የሚወርዱት ከሥልጣን የሚሻሩት በሞት ሲለዩና የሃይማኖት ሕፀፅ ሲገኝባቸው ብቻ ነው፡፡
 • እንደ ጥንቱ ሥርዐት ከኾነ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት መዓርገ ክህነት የሚሰጠው በአብዛኛው ትሩፋትን፣ አገልግሎትን፣ ቅድስናን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት አባቶች ያኖሩትን ትምህርት በመጣስ አንድ ሰው አምኛለኹ፤ በቅቻለኹ ብሎ ቢቀርብ እንኳ ቤተ ክርስቲያን መሾም የለባትም፡፡ቤተ ክርስቲያን ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ መዓርግ በታማኝነት ሊያገልግሏት የሚችሉትን አገልጋዮች በጥንቃቄ መምረጥ አለባት፡፡
 • የአበውን ትውፊት በመጣስ የዕድሜንና የአገልግሎትን ኹኔታ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ ቢሾሙ በዲያቢሎስ ሽንገላ በትዕቢት እየተነፉ እነርሱም ሳይገለገሉ ቤተ ክርስቲያንንም ሳያገለግሉ የጥፋት መሣርያ ይኾናሉ፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያንን ሥሯን መሠረቷን የሚያውቁ፣ በገድልና በትሩፋት፣ በትምህርትና በቅድስና ሕይወት ጸንተው የኖሩትን አባቶች ከገዳማት ጭምር እየፈለገች መሾም ይጠበቅባታል፡፡ በቅድስናቸው የተመሰከረላቸውን አባቶች መሾም በእውነት ምእመናንን በጸሎታቸው የቅድስና ሕይወታቸው ተካፋይ ያደርጋቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በአግባቡ ያላገለገሉ፣ በገዳማዊ ሕይወት ያልተፈተኑ ሰዎችን ያለምንም መስፈርት መሾም ሐዋርያው እንደተናገረው በዲያቢሎስ ነቀፋና ወጥመድ ይወድቃሉ፤ አደጋውም የበዛ ሊኾን ይችላል፡፡

ምንጭ: ሐራ ዘተዋሕዶ

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s