ሰበር ዜና – ጠቅላይ ቤተ ክህነት በአጥማቂ ነኝ ባዩ ግርማ ወንድሙ ላይ የተላለፈውን እግድ አጸና!

 

 • ውሳኔው የአጥማቂ ነኝ ባዩን ሥርዐተ አልበኝነት ሲቃወሙና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ለማስከበር ሲጋደሉ ለቆዩት የደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ሰንበት ት/ቤት አባላትና ምእመናን ታላቅ ድል ነው፡፡
 • ሰንበት ት/ቤቱ እና ምእመናኑ የውሳኔውን አፈጻጸም በቀጣይነትና በጋራ ሊከታተሉ ይገባል
 • ሕገ ወጥ ሰባክያንና አጥማቂ ነን ባዮች ችግር የሚፈጥሩባቸው ሌሎች አጥቢያዎችስ ከዚህ ምን ይማራሉ?BeteKihnet banned Girma

የልዑል እግዚአብሔር ቸርነትና አዳኝነት ከሚገለጥባቸው ምክንያቶች ወይም መንገዶች አንዱ ጠበል ነው፡፡ በገዳማትና አድባራት ቅጽር፣ በቅጽሩ ዙርያና በአካባቢው ሰበካዎች ባሉ የጠበል ቦታዎች በፍጹም እምነት የሚቀርቡ ምእመናን በጠበል እየተጠመቁ ፈውስ ያገኛሉ፤ የእግዚአብሔር ደገኛ ተኣምራት እየተገለጸ ምሕረቱ የተደረገላቸው ሁሉ በየጊዜው ድንቅ ሥራውን እየመሰከሩ ይገኛሉ፡፡

በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ማጥመቅ የሚችለው የቅስና ሥልጣነ ክህነት ያለው አባት ብቻ ነው፡፡ ቅስና የሌለው ሰው አያጠምቅም፤ አይናዝዝም፤ አይባርክም /ፍት.ነ.ፍ.መ.አን.3 ቁ.21/ ቅዱሱን ቅባት መቀባት የሚችለው የክህነት ሥልጣን ያለው ብቻ ነው፡፡ /ያዕ.5÷14/ ሀብተ መንፈስ ቅዱስ በገንዘብ አይሸጥምና አጥማቂው ካህን መማለጃ መቀበል አይገባውም፡፡ /ፍ.ነ.ፍ.መ.አን.7/

በምሥራቅ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ሰባኬ ወንጌልና አጥማቂ ነኝ፤ የፈውስ ጸጋ አለኝ››የሚለው ‹መምህር› ግርማ ወንድሙ፣ ‹‹ለደብሩ ልማት ገንዘብ ለማሰባሰብ›› በሚል ከአንዳንድ የደብሩ አስተዳደር አባላት ጋራ በጥቅም በመተሳሰር ሲያካሂድ የቆየው ‹‹የጠበል አገልግሎት›› ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚፃረር የግል ጥቅም ማካበቻ ነበር፡፡

የ‹‹መምህር›› ግርማን ሕገ ወጥነት ለማጋለጥ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ለማስከበር የተለያዩ ጥናቶችን ሲያደርግ የቆየው የደብሩ ሰንበት ት/ቤት ያሰራጨው መረጃ እንደሚጠቁመው አጥማቂ ነኝ ባዩ ‹‹መምህር›› ግርማ:-

 • የቅስና ሥልጣነ ክህነት አልነበረውም /በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ፊት ቀርቦ ሲጠየቅ አለኝ የሚለው ከዲቁና ያለፈ አይደለም፤ እርሱም ቢኾን ሳይገባው ያገኘው ነው/፡፡
 • ከቅ/ሲኖዶስ ዕውቅና ውጭ በዓለም ፋብሪካ የተመረተ ለፀጉር ድርቀት መከላከያ የኾነውን የወይራ ዘይት ‹‹ቅባ ቅዱስ ነው›› በማለት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዐጸ ውስጥ በማከፋፈልና በመሸጥ ቤተ ክርስቲያንን የንግድ ማእከል አድርጓታል፡፡
 • ለ‹‹መምህር›› ግርማ ፈውስ ሁሉ የሚከናወነው በጩኸት ነው፡፡ ጩኸት ከሌለ ፈውስ የለም ብሎ ያምናል፡፡ አጋንንት ያልጮኸለት ሰው ገና የፈውሱ ጊዜ እንዳልደረሰና በእርሱ ላይ ርኩስ መንፈስ እንዳለበት፣ እንዲገለጥና እንዲወጣለት ራሱን በራሱ በመቁጠሪያ እንዲደበድብ ይነግረዋል፤ ‹ትምህርት› ይሰጠዋል፡፡ አካል ጉዳተኛው ሁሉ አጋንንት እንደያዘው ሰው እንዲጮኸ ይደረጋል፡፡ ግርማ÷ደዌ ዘዕሴት፣ ደዌ ዘአኮቴት፣ ደዌ ዘኀጢአት ለግንዛቤ ያህል እንኳ በውል ለይቶ አያውቃቸውም፡፡ ሕሙማን ከተፈወሱ በኋላ ደዌያት በኃጢአታቸው ምክንያት ብቻ እንደሚመጡ እንደ ምክር ይነግራቸዋል፤ እንዲህም እንዲያምኑ ይገደዳሉ፡፡
 • በተለያየ በሽታ ተይዘው መዳንን ሽተው የሚመጡ ሕሙማን ኃጢአታቸውን በዐደባባይ እንዲናዘዙ ያደርጋል፡፡ የብዙ ሕዝበ ክርስቲያንን ገመናና ኃጢአት ሕሙማኑ ዐውቀውም ይኹን ሳያውቁ ገቢ ማስገኛ እንዲኾን በቪዲዮ አስቀርጾ በቪሲዲ ለገበያ አውሎታል፡፡ አስገራሚው ነገር ‹‹ትዕይንቱን›› በቪዲዮ መቅረጽ የሚችለው እርሱ ያቋቋመው የግል ስቱዲዮ ብቻ ነው፡፡
 • ‹‹ጠበል ብቻውን መጠመቅ ዋጋ የለውም፤ በመቁጠሪያ ራሳችኹን ካልደበደባችኹ›› በማለት ምእመኑ ‹‹ቅባቅዱስ ነው›› ብሎ ከሚሸጠው የፋብሪካ ወይራ ዘይት በተጨማሪ መቁጠሪያ እንዲገዛ ያስገድዳል፡፡ እርሱ ከሚሸጠው መቁጠሪያ ውጭ ሌላው ዋጋ እንደሌለው ይሰብካል፡፡
 • የመዳን ተስፋ ይዘው ከየአህጉረ ስብከቱ የሚመጡ ምእመናን መጠለያ አጥተው በመጉላላታቸው ለተጨማሪ በሽታ የተጋለጡ፣ በመቁጠርያ በመደብደባቸውና የወይራ ዘይት ጠጡ እየተባሉ በመገደዳቸው ለኅልፈት የተዳረጉ ሕሙማን አሉ፡፡
 • መኖርያ ቤቱ ሀብተ ፈውስ እንዳላቸው ደገኛ አባቶች በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ተጋድሎ ተወስኖ ሳይሆን በ1.5 ሚልዮን ብር ወጪ የተገነባ ነው፡፡
 • ግርማ ሰይጣንን አስወጣለኹ ከሚልበት የ‹‹ፈውስ መንገድ›› አንዱ በፕሮቴስታንታዊ ዘይቤ ሕሙማንን በቦክስ እና በጥፊእየተማታ ነው፡፡ የማጥመቁ መርሐ ግብር ሲጀመርም ኾነ ሲያበቃ በጸሎት ፈቃደ እግዚአብሔር ተጠይቆበት አያውቅም፡፡ አባቶቻችን ሲያጠምቁ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ በቃለ እግዚአብሔር አጋንትን በማቃጠል፣ በቅዱስ መስቀል በመዳሰስ፣ ጠበል በመርጨትዳግመኛ ወደ ሕሙሙ እንዳይደርስ በማድረግ ነው፡፡ /ሉቃ.8÷26-33፤ 2ነገ.5÷8-19፤ 1.ቆሮ.1÷18/
 • ‹‹እኛ የምንጨነቀው ሰውን ለማዳን እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ሥርዐት አይደለም፤›› በማለት በሰንበት ቀን ስግደት ያዛል፤ በቤት መቅደስ ሥርዐተ ጸሎት እየተካሄደ /ቅዳሴ እየተቀደሰ፣ ማሕሌት እየተቆመ፣ የደብሩ ክብረ በዓል እየተደረገ/ እርሱ ሌላ መርሐ ግብር ያካሂዳል፤ ይጮኻል፤ እልል እንዲባል ያደርጋል፡፡
 • በማጥመቅ ወቅት÷ ‹‹ርኵስ መንፈስ ያደረባችኹ እገሌ ወይም እገሊት መተት አድርጋባችኹ ነው፤ በእገሌ ወይም እገሊት ዐይነ ጥላ ተደርጐባችኹ ነው፤ በእገሌ ወይም እገሊት አስማት ተደርጐባችኹ ነው›› እየተባለ ምእመናን ከብዙ ጊዜ ዘመዶቻቸው፣ ባልንጀሮቻቸው፣ ጎረቤቶቻቸው እንዲጣሉ፣ ቤት እንዲለቁ፣ ሥራና ትምህርታቸውን እንዲያቆሙ ተደርጓል፤ ሕጋዊ ባለትዳሮች ጋብቻቸው ፈርሶ ተለያይተዋል፤ ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ ፈጥሯል፡፡
 • በተሰጠው ጸጋ፣ እግዚአብሔርን ማክበር ሲገባው ‹‹እኔ እንደዚህ ነኝ›› በማለት ያወራል፡፡ በየመድረኩ የሚያስተምሩም ኾነ አጋንንት ያደረባቸው ሕሙማን እንዲመሰክሩለት ያደርጋል፡፡ በአጠቃላይ የእግዚአብሔር ክብር ከሚወራ ይልቅ አለኝ የሚለው ቅድስና እንዲለፈፍለት ያደርጋል፤ ራሱም ስለራሱ ይናገራል፡፡
 • በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ማንም ሰው በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ለግል ጥቅም የሚውል ምንም ዐይነት ንግድ ማካሄድ የለበትም፡፡ ‹‹መምህር›› ነኝ ባዩ ግርማ ግን በቤተ ክርስቲያን ቅጽር ለራሱ ገቢ ማስገኛ የሚውሉ ሌሎች ንግዶችን ይነግዳል፡፡ በዚህም በአንድ ቀን ብቻ ከብር 25,000 – 28,000 ገቢ ይሰበስባል::
 • ከንግዱ ባሻገር ከጠበል አገልግሎት የሚገኘውና በስእለት፣ በስጦታ የሚሰበሰበው ገንዘብ በአግባቡ ለቤተ ክርስቲያን ገቢ መኾን ሲገባው ለአጥማቂ ነኝ ባዩ በፐርሰንት የሚሰጥበት አሠራር አስተክሏል፡፡
 • ግለሰቡ ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ውጭ በሚፈጽማቸው በእኒህና በመሳሰሉት ሕገ ወጥ ተግባራት ከእርሱ ጋራ የጥቅም  ግንኙነት ካላቸው አንዳንድ የሰበካ ጉባኤ አበላት በቀር /በወር 8000 ብር እጅ መንሻ የሚታሰብላቸው እንዳሉ ይነገራል/ ስንኳን የደብሩን የልማት ጥረት በገቢ ሊደግፍ ማኅበረ ካህናቱን የሥራ ዋስትና በማሳጣት ስጋ ለመከፋፈል ሞክሯል፡፡
 • በደብሩ ሰንበት ት/ቤት የሚካሄደው ተከታታይ ትምህርት አጥማቂ ነኝ ባዩ በሚፈጥረው መሰናክል ምክንያት እየተቋረጠ ወጣቶች የመበተን ስጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡
 • የደብሩ አስተዳደር በዚህ ጉዳይ ላይ የሚመጡ ማንኛውንም ጥያቄዎች አላስተናግድም በማለት በሩን ዘግቶ ቆይቷል፡፡ በምትኩ በሰ/ት/ቤቱ አባላት ጥረት በብዙ ልመና እንዲያናግሩ በተደጋጋሚ በደብዳቤ ቢጠየቁም አሁንም እንደተለመደው ጥያቄውን ውድቅ አድርገዋል – ጥበቃ በመጥራት፣ ከቢሮ በግዳጅ ለማስወጣት በመሞከርና ለፖሊስ እንደውላለኹ ብለው በማስፈራራት፡፡ በመጨረሻም ይለይላችኹ በማለት ‹‹ምንም የገቢ ምንጭ ስለሌለን አጥማቂውን ከነሕጸጻቸው እንቀበላቸዋለን›› በማለት በድፍረት አሳውቋል፡፡ ከደብሩ ሰ/ት/ቤት ተወክለው ያነጋገሯቸውን የሰ/ት/ቤቱን አባላት÷ ‹‹ጋጠ ወጦች፣ ዐላዋቂዎች፣ የቤተ ክርስቲያኑን ዕድሳት የምታስተጓጉሉ›› በሚሉ ዘለፋዎች ከሰበካ ጉባኤው አባላት ጋራ መልካም ግንኙነት እንዳይኖራቸው ተደርጓል፡፡
 • ከ‹‹ማጥመቅ›› አገልግሎቱ በኋላ በጎ ፈቃደኞች ቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑን ሲያጸዱ የሚታየው የንጽሕና ጉድለት አስከፊ ነው፡፡ የደብሩ መጸዳጃ ቤት ከብልሽት አልፎ ለቤተ ልሔሙ አገልግሎት ዕንቅፋት ቢኾንም ይህ ‹‹መምህር›› ግርማን ጨርሶ አይገደውም፡፡
 • ሰንበት ት/ቤቱ ከላይ የተገለጹትንና ከደብሩና ሌሎች ስፍራዎች በቪዲዮ እና በድምፅ እንዲሁም በጽሑፍ የተገኙ መረጃዎችን በመያዝ ሙሉ ማስረጃውን ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ካቀረበና በጉዳዩ ላይ ከደብሩ አስተዳደር ክፍሎችና ከሰ/ት/ቤቱ አባላት ጋራ ለሰዓታት ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ይህን ተከትሎ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ‹‹መምህር›› ግርማ ወንድሙን በሰኔ ወር፣ 2003 ዓ.ም ጠርቶ ካነጋገረው በኋላ፣ ከዲቁና ያለፈ ክህነት ሳይኖረው የፈጸመው ተግባር ከፍተኛ ድፍረት የተመላበት ስለኾነ የማጥመቅ ሥራው በአስቸኳይ እንዲቋረጥ እንዲደረግና አፈጻጸሙ እንዲገለጽለት በቁጥር 4290/90/03 በቀን 8/10/2003 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ የደብሩን አስተዳደር አዝዞ ነበር፡
 • በትእዛዙ መሠረት የደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ‹‹መምህር›› ግርማ ወንድሙ ከሕገ ወጥ ተግባሩ እንዲገታ በደብዳቤ ቢያሳውቀውም ውሳኔው በሙስና /የጥቅም ትስስር/ ተፈጻሚ ባለመኾኑ አገረ ስብከቱ ለአዲስ አበባ ከተማ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ፣ ለደምበል ፖሊስ ማዘዣ ጣቢያ እና ለፌዴራል ፖሊስ በጻፋቸው ደብዳቤዎች ለማሳወቅ ተገዶ ነበር፡፡
 • እነኾ ዛሬ የሰንበት ት/ቤቱ፣ የሌሎች አገልጋዮችና ቀናዒ ምእመናን ጥረት ሠምሮ ደብሩ በቁጥር 339/ቀ/አ/ቤ/ክ በ28/8/2005 ዓ.ም በግርማ ወንድሙ ላይ በድጋሚ ያስተላለፈው እገዳ በመንበረ ፓትርያሪኩ የበላይ ውሳኔ ሊጸና ችሏል፡፡ አፈጻጸሙን ሁሉም አካላት በመተባበር ሊከታተሉት ይገባል፡፡ በሀገር ውስጥ ይኹን በውጭ አህጉረ ስብከት የሚገኙ ሌሎች አጥቢያዎችም የሕገ ወጥ አጥማቂዎችንና ሰባክያንን ስምሪት በማጋለጥና በመግታት ረገድ ከደብሩ ሰንበት ት/ቤትና ምእመናን ሊማሩ ያስፈልጋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን                  ቁጥር፡-9474/756/2005 ዓ.ም

መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት                                     ቀን፡- 8/9/2005 ዓ.ም

 

ለደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ክ ሰ/ጉ/ጽ/ቤት

አዲስ አበባ

 

ጉዳዩ፡- በአስቸኳይ አጥማቂ መምህር ግርማ ወንድሙ በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ጉ/ጽ/ቤት በቁጥር 339/ቀ/አ/ቤ/ክ በ28/8/2005 ዓ.ም የተሰጠው እገዳ መ/ፓ/ጠ/ጽ/ቤት ያጸናው ስለመኾኑ ይመለከታል፤

መ/ር ግርማ ወንድሙ ሰባኬ ወንጌልና አጥማቂ ነኝ፤ የማዳን ፈውስ አለኝ በማለት በሕገ ወጥ መንገድ እስከ አሁን ድረስ በደብሩ እያጠመቁ ይገኛሉ፡፡

ይኹንና በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከ1993 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ በየወቅቱ በሕገ ወጥ መንገድ የማዳን ፈውስ አለኝ በማለት ሕዝበ ክርስቲያኑን በየደብሩ ቅጽር ግቢ በማሰባሰብ የሚያጠምቁትን በተመለከተ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

 1. ከቤተ ክርስቲያኗ ቀኖና ሥርዐት ውጭ በሚፈጸም ስብከትና ጥምቀት
 2. የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሳይፈቅዱ የሚሰጥ የወንጌልና ጥምቀት አገልግሎት መስጠትን በተመለከተ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነ ቢኾንም በሥርዐተ አልበኝነት በተለያዩ ቦታዎች የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሲጣስ ይታያል፡፡

በመኾኑም መምህር ግርማ ወንድሙ በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የሚፈጽሙትሕገ ወጥ የማጥመቅ ሥርዐትና የወንጌል አገልግሎት መኾኑን እየገለጽን የእምነታችን ተከታይ ሕዝበ ክርስቲያኑ ከዚህ እግድ ጋራ በተያያዘ የጸጥታ ችግር እንዳይገጥመው የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ጥብቅ ክትትል በማድረግ ውሳኔውን ተግባራዊ እንዲያደርግ እያሳሰብን የሚመለከታቸው የመንግሥት የጸጥታ አካላትም የቤተ ክርስቲያኒቱን ውሳኔ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ አስፈላጊው ትብብር እንዲያደርጉልን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን

ግልባጭ

 • ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
 • ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ ልዩ ጽ/ቤት
 • ለአስተዳደር መምሪያ
 • ለሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
 • ለምሥራቅ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት
 • ለፌዴራል ጉዳዮች ጽ/ቤት
 • ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
 • ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት
 • ለአ/አ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን
 • ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ
 • ለአ/አ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ
 • ለቂርቆስ ክ/ከ ፍት ጽ/ቤት

         አዲስ አበባ፤

 

የደብሩ አስተዳደር በ‹‹መምህር›› ግርማ ላይ የጻፈው ደብዳቤ

ni

 

 

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

Advertisements

3 thoughts on “ሰበር ዜና – ጠቅላይ ቤተ ክህነት በአጥማቂ ነኝ ባዩ ግርማ ወንድሙ ላይ የተላለፈውን እግድ አጸና!

  1. yetewahedobet Post author

   የተከበሩ (Anonymous) ለመሆኑ ስለቤተክርስቲያን ምን ያህል እውቀት እንዳሎት ባናውቅም ነገር ግን እኛም ሆንን ሌሎች ‘መምህር ግርማን’ የሚቃወሙት በከንቱ እርሶ እንዳሉት በሌላ ጥላች ወይንም በእርሳቸው ሥራ እንዳይሰሩ የበሐር ዛፍ ጠባይ ይዞን እንዳይመስሎት፥ እርሶ የእዛ ጠባይ ካሎት ቢተውት እንመክራለን አልያ ግን እኛም ሆንን ሌሎች እንደሚሉት መምህሩ በእርሳቸው የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አድሮ ሥራ ሊሰራ እንደሚችል እናምናለን ነገር ግን በእራሳቸው ጥበብ እና ብቃት እንደሚሰሩት ካመኑ ወይንም ማሳየት ከሞከሩ ሰውየው እራሳቸው ነገ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንዳይሉ ያስፈራል።
   ቀላል ምሳሌ እንስጥዎት ለግንዛቤ እንዲረዳዎት ወይን ለሌች አንባቢያን በአጠቃላይ፡ ቀደምትቅዱሳን፣ ሰማዕታት፣ ሐዋርያት፣ እንዲሁም ፃድቃን በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው በርካታ ታዓምራት እና ሥራዎችን ሰርተዋል ለመጥቀስ ያህል ሙታንን አስነስተዋል፣ እውራንን አብርተዋል፣ ሽባን ተርትረዋል፣ ሰማይን ዓመታት ዝናም እንዳይሰጥ ለጉመዋል . . . ወዘተ እንዲህ አይነት ድንቅ ተዓምራትን ሲሰሩ ወይም የሰሩት የቀደሙት ጻድቃን አንድም ቀን እኛ አደረግነው ወይም እኛን ተከተሉ ብለው አያውቁም እንዲያውም ለተከታዮቻቸው እንኳን እግዚአብሔር ፈቃዱ ቢሆን ብለው ነበር የሚናገሩት ነገር ግን አንድም ቀን እናደርገዋለን ወይም ይሄ ይደረግለሃል ብለው በመንፈስ ቅዱስ ተዘባብተው አያውቁም እንዲህ በአሁን ሰዓት በመምህሩ እና መሰሎቹ የሚሰራው ሥራ ሁሉ ፕሮቴስታንታዊ እንደሆነ ልንገነዘው ይገባል በመጀመሪያ ልናውቀው የሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በርካታ ቦታዎች በእግዚአብሔር ፈቃድ ቃል ኪዳን ያላቸው በእነሱ ያመነ እና የተማጠነ ርስተ መንግሥተ ሰማያትን እንደሚወርሱ በመጽሐፍ ተጠቅሷል “በጻድቁ ስም ቀዝቃዛ ውሃ ያጠጣ የጻድቁን ዋጋ ያገኛል” ለምሳሌ የጻድቁ አባታችን አቡነ መልከጼዲቅ ገዳም ባለው ቃል ኪዳን መሰረት ሞቶ በገዳሙ ገረገር እንኳ የተቀበረ ሥጋው እንደማይፈርስ ቃል ኪዳን የገባላቸው ቅዱሳን ስለሆኑ እስከ አሁን አሉ ገዳሙም ያን ቃል ኪዳን ከመድኅኒዓለም ተቀብሎ በርካታ ተዓምራት እየተፈጸመባቸው ነው። ሌሎች በርካታ የጸበል ቦታዎችም አሉ በርካቶችም ከህመማቸው ፈውስን ከወደቁበት ኃጢያትም ስርየትን ያገኙባቸው እነዚህ የቅዱሳን ቦታዎች ሁሌም ቅዱስ ስለሆኑ ቦታው ሁሌም ይፈውሳል ነገር ግን አጥማቂው አይደለም የሚፈውሰው ብዙዎች እየሳትን እና እየወደቅን ያለንው አጥማቂው ነው ብለን ስለምናምን ነው፣ አጥማቂው ለቦታው ተጨማሪ በረከት ይሆነዋል እንጂ ያ አጥማቂ ነረም አልኖረም ጸበሉ ግን የማዳን ሥራውን ሁሌም ይሰራል።
   ወደ መምህሩ ስንመጣ ግን “ኑ እቤቴ ወስጄ አጠምቃችኋለው” በማለት የዋሃን ምዕመናን በሰውየው ቤት በመሄድ በጸበሉ ሳይሆን በሰውየው እንድንደገፍ እያደረጉ ያሉና የቤተክርስቲያኒቱን ፍጹም አስተምህሮ የሚፋልሱ ጎጠኛ ሰው እንደሆኑ ልንገነዘብ ይገባል። ይባስ ብለው ኑ ሥራዬን ተመልከቱ በማለት በDVD በማሳተም በእግዚአብሔር ሥራ እና ተዓምራት ትርፍን እና የራስን ዝናን በማደራጀት ላይ እንዳሉ ልንገነዘብ ይገባል። እነ ቅዱስ ጳውሎስ በጥላቸው ሙታንን ሲያስነሱ፣ በጨርቃቸው ሽባ ሲተረትሩ ከእኛ የሆነ ምንም የለም እኛ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተቃኝተን የእርሱ የሆነውን የምንሰራ የእግሩን ጫማ እንኳን የማንደርሰ ነን በማለት ነው የሚናገሩት። እኛ አደረግነው ሽባን ተረተርን ብለው ተናግረው አያውቁም ምናልባት “ግብረ ሐዋርያትን” ቢያነቡት በርካታ መልስ ማግኘት ይችላሉ ለጥያቄዎ።
   የሆነ ሆኖ እኛም ሆንን ሌሎች ከመምህሩ ጋር የግል የሆነ ነገርም ወይንም ሌላ የለንም የቅድስት ቤተክርስቲያናችን ህልውና ግን እንድንናገር እና እንድንመሰክር ግድ ይለናል እንጂ እርሶ እንዳሉት ወይም እንዳሰቡት በሳቸው ላይ የተለየ ነገር የለንም ለእርሶም የዓይን መግለጫ እንዲሆኖት እስቲ DVD ብለው ያዘጋጁትን ተመልከቱት የእግዚአብሔርን ድንቅ ማዳን ተመልከቱ ነው ወይስ የ’መምህር ግርማን’ ድንቅ የማዳን ስራ ተመልከቱ ነው የሚለው??? ለማንኛውም እርሳቸው ዛሬ ያሉ ነገ የሌሉ ሰው ናቸው ትላንት የነበረች ነገም እኛና እርሶ አልፈን የማታልፈውን ቅድስት ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ብቻ እንመልከት አምልኮታችን እንዳይበረዝ በምዕራባውያን ተጽዕኖ እንዳይኖርብን እንጠንቀቅ ትላንት እኮ እኔ ክርስቶስ ነኝ ብሎ የተነሳ አለ ነበር፣ መምህሩም ኑ ማዳኔን ተመልከቱ ካሉ ነገስ? በቤታቸው ወስዶ ማጥመቅስ ለምን አስፈለገ?? በቤታቸውስ ምን እየተደረገ እንደሆን ምን እናውቃለን?? ሴቶች እህቶቻችን ለበርካታ ዓመታት በእንዲህ ዓይነት አሳሳዮች በርካቶች ተበላሽተዋል፣ እምነታቸውንም ክደዋል፣ ላልተፈለገ ችግር ውስጥ ወድቀዋል ነገር ግን በቤተክርስቲያን ቅጽር የሆነ ከሆነ
   1ኛ/ ፈርሃ እግዚአብሔር ይኖራል በሌላ ሃጢያት የመውደቅ ሃሳብ ላይኖር ይችላል
   2ኛ/ በርካቶች ስለሚኖሩ ምስክር ሊሆኑ ይችላሉ
   3ኛ/ ሥራው የሚሰራው በአጥማቂው ሳይሆን በቅዱሳኑ እና በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መሆኑን እንማራለን እናስተምራለን
   ነገር ግን ኑ እቤቴ የማዳን ሥራ እሰራለሁ እያሉ ብዙ ክህደት እያስተማሩ እንዳሉ ልንገነዘብ ይገባል እንላለን
   ለዛሬ ይቆየን

   Reply

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s