የሕማማት ዋዜማው ሕማም! የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ተቋማዊ ህልውና እና የክህነታዊ ሥልጣን ማእከላዊነት በምዝገባና ፈቃድ ዕድሳት በሚሸረሽር እና በሚያፋልስ የመመሪያ ረቂቅ ላይ እየተመከረ ነው

 

 • ቤተ ክርስቲያን በፍትሐ ብሔር ሕጉ ያገኘችውን ሕጋዊነት የሚከልስ፣ ታሪካዊ ክብሯን የሚያንኳስስ፣ ማኅበራዊ እሴቷን የሚቀንስና አሐቲነቷን የሚያፈርስ በምትኩ የመንግሥትን የቁጥጥር አቅም የሚያፈረጥምና የሚያነግሥ ነው፡፡
 • የሃይማኖትና መንግሥት ግንኙነትን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የሚጥስ መመሪያ ነው
 • የሃይማኖት ተቋማትን ልዩ መንፈሳዊና ድርጅታዊ ጠባይ ያገናዘበ መመሪያ አይደለም
 • መመሪያው ለአድልዎና ብልሹ አሠራር የመጋለጥ ዕድሉ የሰፋ ነው
 • መመሪያው የአሐቲ ቤተ ክርስቲያንን መርሕ በመጣስ የፕሮቴስታንቲዝምን ራስ በቀል ዘይቤ የሚያስፋፋ ነው፡፡
 • ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ያሳዘነውና የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን ጨምሮ የሕግ ምሁራንን ያነጋገረው የመመሪያው ረቂቅ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ዐበይት አጀንዳዎች አንዱ እንደሚኾን ተጠቁሟል

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ‹‹የሃይማኖት ተቋማትን ለመመዝገብ›› በሚል በቅርቡ ለውይይት የዘረጋው የመመሪያ ረቂቅ፣ በአገራችን ታላቅ ፋይዳ ያላቸውን የሃይማኖት ተቋማት ልዩ መንፈሳዊ ጠባይ እና ድርጅታዊ አሠራር ያላገናዘበ በተለይም ጥንታዊትና ብሔራዊት የኾነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ሰውነት የሚከልስና ማእከላዊ አሠራሯን የሚያፈርስ እንደኾነ እየተገለጸ ነው፡፡

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዐዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀጽ 14/1/ሸ የተሰጠውን ሥልጣንና ተግባር ለመወጣት በሚል መዘጋጀቱ የተገለጸው የመመሪያው ረቂቅ፣ አስፈላጊ የኾነባቸው አራት ነጥቦች በመግቢያው ላይ ተመልክተዋል፡፡ ከእኒህም ዋነኛው ‹‹ለሃይማኖት ወይም እምነት ተቋማት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠው÷ የሃይማኖት ነጻነት፣ እኩልነትና የመደራጀት መብት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ለማስቻልና ነጻነታቸው እንደተጠበቀ ኾኖ አሠራራቸው ከሕገ መንግሥቱና ከሌሎች የአገሪቱ ሕጎች ጋራ በተጣጣመ ኹኔታ እንዲቀጥል ለማድረግ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ነው፤›› በሚል ሰፍሯል፡፡

ከሁሉ በፊት በጉዳዩ ተከታታዮች አስተያየት÷ የሃይማኖት ወይም እምነት ተቋማት ጠባይ በመሠረቱ መንፈሳዊ፣ በየ‹‹መጽሐፋቸው›› የሚመራና ከ‹‹የመጽሐፋቸው›› በሚመነጭ ሥርዐት የሚተዳደር ኾኖ ሳለ ‹‹አሠራራቸውን ከሕገ መንግሥቱና ከሌሎች የአገሪቱ ሕጎች ጋራ በተጣጣመ ኹኔታ እንዲቀጥል ማድረግ›› የሚለው የተቋማቱን አስተምህሮ ሊጋፋና ለአድልዎ የተጋለጠ ሊኾን ይችላል፡፡

‹‹ክትትልና ድጋፍ ማድረግ›› በሚል በመመሪያው ረቂቅ ላይ የተዘረዘሩት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሥልጣንና ተግባራትምሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ እንደኾኑና አንዱ በሌላው ጣልቃ እንደማይገባ የሰፈረውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የሚቃረን ነው፡፡ በምትኩ መንግሥት በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና በስቭል ማኅበራት ላይ ባወጣው ሕግና በሚያካሂደው ቁጥጥር አገባብ የቁጥጥር አቅሙን የሚያፈረጥምበት ሊኾን እንደሚችል ተመልክቷል፡፡

ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው ሚኒስቴሩ በዚህ መመሪያ የሚከተለው የክትትልና ድጋፍ አሠራር ‹‹ልማት ዴሞክራሲና የሃይማኖት አክራሪነት›› በሚል ርእስ በተለያዩ መድረኮች ከሚሰጣቸው ሥልጠናዎች አንጻር፣ ‹‹በሃይማኖት ተቋማቱ የአሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በማድረግ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ለሃይማኖት አክራሪዎች ምቹ ኹኔታ እንዳይፈጥር አብሮ ለመሥራት››የሚጠቅም መኾኑን ይናገራሉ፡፡

ዴሞክራሲን የልማት መሣሪያ አድርጎ ለሚመለከተው መንግሥት፣ የዜጎች ነጻነት የዴሞክራሲያዊ መብቶች አካል እንደኾነ የሚኒስቴሩ ሰነዶች ይገልጻሉ፡፡ ሰነዶቹ እንደሚያትቱት÷ በሁሉም ሃይማኖቶች መመሪያዎች[አስተምህሮዎች] እና በመንግሥት የዴሞክራሲ ድንጋጌዎች መካከል አንዳችም ተቃርኖ የለም፤ ያልተመለሰ የሃይማኖት የመብት ጥያቄም የለም፡፡ ስለዚህ ሃይማኖትን ተገን አድርጎ መነሣት ዓላማው ሌላ በመኾኑ ይህ የአክራሪዎች አፍራሽና ስውር አጀንዳ ቦታ እንዳያገኝ፣ ኅብረተሰቡ በድህነት ላይ የጀመረውን ትግል በተረጋጋ መንፈስ እንዲቀጥልበጋራ መታገል ያስፈልጋል፡፡

የሃይማኖት ወይም እምነት ተቋማትን የገቢ ምንጭ መሠረትና የሚውልበትን ተግባር፣ የመሪዎቻቸውን ማንነትና አሿሿም እንዲሁም የሥራ ክንውንና የኦዲት ሪፖርታቸውን በዝርዝር ከማወቅ አልፎ በ‹‹ማስተካከያ ርምጃ›› ከምዝገባ እስከማገድና ሕጋዊ ሰውነትን እስከማሳጣት ድረስ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሥልጣን የሚሰጠው የመመሪያው ረቂቅ የጋራ መታገያ ሰነድ ይኾን?

በአለቃ አያሌው ታምሩ አነጋገር ‹‹ነዋሪ ባለርስት ስንዱ እመቤት›› ለኾነችው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመመሪያው ረቂቅ ራሱ አይመለከታትም፤ በእርሷም ላይ ተፈጻሚ ሊኾን አይችልም፡፡ ለምን? የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሕግ የተቋቋመችው በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ ነው፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ (3) ምዕ. (1) ቁጥር 398 ንኡስ ቁጥር (1)÷ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በሕግ በኩል እንደ አንድ ሰው የምትቆጠር ናት›› ሲልሕጋዊ ሰውነት ሰጥቷል፡፡ በዚሁ ቁጥር 398 ንኡስ ቁጥር (2)÷ ‹‹እንዲህ እንደ መኾኗ በመሥሪያ ቤቶቿ አማካይነት በአስተዳደር ሕጎች የተፈቀዱትን መብቶች ሁሉ ልታገኝና ልትሠራባቸው ትችላለች›› ቤተ ክርስቲያናችን ሕጎችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በራሷ በማውጣት ራሷን ማደራጀትና መምራት እንደምትችል ደንግጓል፡፡Sebeka Gubae General Structure

ይህ ሕግ በሌላ ሕግ፣ ዐዋጅ ወይም ደንብ አልተሻሻለም፡፡ በዚያውም ላይ በፍትሕ ሥርዐቱ የሕግ አወጣጥ መርሕ ይህ ሕግ፣ ይህ ድንጋጌ በአንድ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤት ሥልጣንና እርሱ በሚወጣው መመሪያ ሊሻሻል ወይም ሊሻር አይችልም፡፡ ስለኾነም የመመሪያው ረቂቅ በራሱ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን አይመለከታትም፤ በእርሷም ላይ ተፈጻሚ ሊኾን አይችልም፤ አይገባም፡፡ ይህን አቋማችንን የሚያጠናክረው የ1952 ዓ.ም ፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 407 ንኡስ ቁጥር (1) እንዲህ ይላል÷ ‹‹ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በቀር ሌሎች አብያተ ክርስቲያን ሃይማኖቶችና ማኅበሮች የሚተዳደሩት እነዚሁኑ በሚመለከቱ ሌሎች ሕጎች ነው፡፡››

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከሃይማኖት ተቋማት ምዝገባ ጋራ በተያያዘ አሠራሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እንደማይመለከታት በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር በአንድ ወቅት በጽ/ቤታቸው ተጠርቶ በነበረ መድረክ ከሌሎች ጋራ ተገኝተው የነበሩ የቤተ ክርስቲያናችንን አባቶች ከመድረኩ በመመለስ (በማሰናበት) ግልጽ አድርገው እንደነበር መነገሩ የሕጉን ድንጋጌ የተረዳ ነው፡፡የቀድሞው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስም የቤተ ክርስቲያኒቱንና በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቿን በመንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የበላይ ተቆጣጣሪነት ሥር አስመዝግቡ የሚሉ ጥያቄዎች በተነሡ ቁጥር የተቀባይነት ዕድሉን ዝግ በሚያደርግ አኳኋን የቤተ ክርስቲያናችንን ልዕልና፣ ብሔራዊነትና ጥንታዊነት ከማስከበር አኳያ የነበራቸው ፈርጣማ አቋም እና ቃለ ተግሣጽ የሚታወስ ነው፡፡

Ethiopia

ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም

‹‹የታላቁ መሪያችንን የበለጸገችና አገርና ሕዝብ ግንባታ ራእይ እናሳካለን›› ከሚሉት የወቅቱ መሪዎች በተለይም የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ግን፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ሕጋዊ ሰውነት የሚሸረሽረውንና በክህነታዊ ሥልጣን ማእከላዊነት ላይ የቆመውን መዋቅራዊ ህልውናውን የሚያፋልሰውን የመመሪያ ረቂቅ ተቀብለን እንድናጸድቅ ይኸው መወትወታቸውን ይዘዋል፡፡ የመመሪያው ረቂቅ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽ/ቤት በተጠራና ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ሦስት አባቶች ከሌሎች እምነቶች መሪዎች ጋራ ውይይት የተካሄደበት ሲኾን ተሳታፊዎቹ በመመሪያ ረቂቁ ላይ ሊካተቱና ሊስተካከሉ ይገባቸዋል የሚሏቸውን ሐሳቦች እንዲያመጡ ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በከፍተኛ የሃይማኖት መሪዎች ደረጃ ከተካሄደው ውይይት በፊት ረቂቅ መመሪያው፣ በአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት እንዲሁም ከመጋቢት 6 – 7 ቀን 2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እና ከኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን ርዳታ ድርጅት ጋራ በመተባበር በሐዋሳ ተዘጋጅቶ በነበረው መድረክ ላይም በየመልኩ መቅረቡ ተገልጧል፡፡ በሁሉም መድረኮች ማለት በሚቻል ኹኔታ ከቤተ ክርስቲያናችን አባቶችና ልኡካን የመመሪያውን ረቂቅ በተመለከተ ሐሳቡ እንግዳና ለመወሰንም ከአቅማቸው በላይ በመኾኑ የቤተ ክርስቲያኒቱን የመጨረሻ አመራር አካል÷ የቅዱስ ሲኖዶስን ሥልጣን እንደሚሻ÷ በአጽንዖት ማሳሰባቸው ነው፡፡   

የመመሪያው ረቂቅ በእያንዳንዱ አንቀጽ ውስጥ የቤተ ክርስቲያናችንን ቀኖናዊነት የሚፃረሩ እና አሐቲነቷን አናግተው ማለቂያ ወደሌላቸውdenominations”  ክፍልፋዮች የሚያዘቅጡ፣ ማኅበራዊና ልማታዊ ሚናዋን በማጥበብ ጎጠኞችንና መናፍቃንን የሚመግቡ ፈንጂ ሐሳቦች የተቀበሩበት ነው፡፡ እነማንና ምን ያህል የሃይማኖት ወይም እምነት ተቋማት በአገራችን እንዳሉ መመዝገብ፣ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ የጥፋት ተግባራት ሲፈጸሙ በበሳል ሃይማኖታዊ አስተሳሰብና በነጻ ተቋማዊ አመራራቸው እንዲፈቱ ማገዝ፣ መብቱን ያስከበረና ግዴታውን የሚወጣ ዜጋ እንዲያብብ በጋራ መሥራት የአባት ነው፡፡

በሐዋሳው የምክክር ስብሰባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ እንደተናገሩት፣ ከመንፈሳዊነት ባሻገር ድርጅታዊ አወቃቀር ያላቸው የሃይማኖት ተቋማት ዘመናዊ የአመራር ስልትን የተመለከተ ሞያዊ ሥልጠና እንዲያገኙ እገዛ ማድረግም የተገባ ነው፡፡ አሁንም ዋና ጸሐፊው እንዳሉት፣ የሃይማኖት ተቋማቱ ሉላዊው ክሥተት ይዟቸው የሚመጡ የባህል ወረራና የማንነት ቀውስ ዓለም አቀፋዊ ጫናዎችንና ግፊቶችን ለመቋቋም በሰላምና በሥነ ምግባር እሴት ግንባታ ላይ ለዜጎች ትምህርት የሚሰጥበት የጋራ ሰነድ ማዘጋጀትም የሚደገፍ ነው፡፡

የእምነት ነጻነትንና የሃይማኖት እኩልነትን በማስከበር እንዲሁም ይህን አስከብራለኹ ተብሎ በሚደረግ ‹‹ክትትልና ድጋፍ›› ስም የሃይማኖት ወይም እምነት ተቋማትን አንድነት የሚያፈራርስ መመሪያ ማጽደቅ ግን የሕገ መንግሥት ጥሰትና ታሪካዊ በደልን ያህል እብሪትና ዐላዋቂነት ነው፡፡ ንጉሡ በተሻሻለው የ1948 ዓ.ም ሕገ መንግሥታቸው ‹‹መሠረታዊት ቤተ ክርስቲያን›› ያሏትን በተግባር ግን ጭቁን የኾነች ቤተ ክርስቲያን የማምከን የ”Neutralizing the Church” ስትራተጂ ሌላው ክትያ እንዳይኾንም ያሰጋል፡፡

ስለ መመሪያው ቃልና መንፈስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እያዘኑበት ነው፤ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና የሕግ ምሁራን እየተነጋገሩበት ነው፡፡ እንደተባለው ረቂቁ በቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ የሚታይ ከኾነ ከዚያ በፊት ሊቃውንቱና ምሁራኑ በዝርዝር የሚሉን ነገር እንደሚኖር ተስፋ እናደርጋለን፡፡

የመመሪያው ረቂቅ፡-

 • ከሐዋርያት ዘመን ሲያያዝ በመጣው ትውፊት መሠረት÷ አንዲት፣ ቅድስት፣ ከሁሉ በላይና ሐዋርያዊት የኾነችው ቤተ ክርስቲያናችን ከአራተኛው መቶ ዓመት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ሐዋርያትና አበው ሊቃውንት በወሰኑት መሠረት አገልግሎቷንና አስተዳደሯን የምትመራበትን ፍትሕ መንፈሳዊ እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የሚያፋልስ ነው፡፡
 • እንደ ዘመኑ ኹኔታ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በየጊዜው ሲኖዶስ እያደረጉ የሐዋርያት ትምህርትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዳይፋለስ ምእመናንን በመንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለመመገብ የወሰኑትን ሥርዐት የሚጥስ፣ በቤተ ክርስቲያን አለመግባባት ሲፈጠር በፍትሕ መንፈሳዊ ብቻ መወሰን ያለበት መኾኑን የማይገነዘብ፣ ቤተ ክርስቲያናችን በጠቅላላው አስተዳደራዊ፣ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ አገልግሎት በኩል በራስዋ ሕግና ሥርዐት በመመራት እንድትሠራ ለማድረግ ቅዱስ ሲኖዶስ በአለው ሥልጣን ያወጣውን ሕገ ቤተ ክርስቲያንና የቃለ ዐዋዲ ድንጋጌ የሚደመስስ ነው፡፡
 • በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውና በቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻው ከፍተኛ ሥልጣን ባለቤት በመኾን ሕጎችን፣ ልዩ ልዩ ደንቦችንና መመሪያዎችን የማውጣት፣ ለጥፋተኞችና ለበደለኞችም ምሕረትና ይቅርታ የመስጠት የዳኝነት ሥልጣን ያለውን የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና /የበላይነት/ የሚጋፋ ነው፡፡
 • ቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊትና ብሔራዊት እንደመኾንዋ ከጥንት ጀምሮ በሊቃውንት ልጆችዋ አማካይነት እየጻፈችና እያዘጋጀች ስትገለገልባቸው፣ ስትጠብቃቸውና ስታስተምራቸው የኖሩትንና በየገዳማቱ፣ በየአድባራቱና በየገጠር አብያተ ክርስቲያኑ ከታቦተ ሕጉ ጀምሮ ያሏትን ንዋያተ ቅድሳት፣ አልባሳት፣ ሥዕላት፣ መጻሕፍትና ልዩ ልዩ ንብረቶች ቤተ መዛግብት ኾና በጥንቃቄ ስትጠብቅ እንደኖረች ኹሉ፣  አሁንም በየሥፍራው በተለያዩ መልኮች የሚገኙትን ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች በባለቤትነት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ፣ ንብረቷንና ይዞታዋን በሕግ ለማስከበር ያላትን መብት የሚገድብ፣ የሚያጠፋ ነው፡፡
 • የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍቅርና አንድነቱን አጽንቶ፣ የሀገሩን ዳር ድንበር ጠብቆ፣ ማንነቱን አክብሮ የኖረው ከቀደምት አባቶች በወረሰው የግብረ ገብነት፣ የአገር አንድነት፣ የሃይማኖት ጽንዓት ነው፡፡ መመሪያው÷ ቤተ ክርስቲያን ይህንኑ ለትውልድ ለማስተላለፍ አስፈላጊ በኾነ ቦታ ሁሉ ትምህርት ለመስጠት፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ፍትሕ ርትዕ እንዲሰፍን ያላትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሚና የሚያደቅ፣ የሚያዋድቅ ነው፡፡
 • ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷን ለማጠናከር በማእከልና በአህጉረ ስብከት ደረጃ የልማትና በጎ አድራጎት ተቋሞችን እንዳታደራጅ፣ ያደራጀቻቸውንም በበላይነት ለመቆጣጠር ያላትን መብትና ሓላፊነት የሚያቅብ፣ በቀጣይም ቤተ ክርስቲያኒቱን ከልማትና በጎ አድራጎት ተግባር የሚያግድ ነው፡፡
 • ለመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ፣ ለአንድነቷና ለአስተዳደሯ ከፍተኛ ሓላፊ የኾኑት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ÷ በርእሰ መንበር ሥልጣናቸው መላው ካህናትና ምእመናን የሚገዙበት መመሪያ፣ ትምህርትና ቡራኬ ለመስጠት፣ በመጀመሪያ ደረጃም ኾነ በይግባኝ የሚቀርቡት ጉዳዮች ሕግና ደንብ በሚያወጣው በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ወይም በቋሚ ሲኖዶስ መመሪያ ወይም የቅዱስ ሲኖዶሱንና የቋሚ ሲኖዶሱን ሕግ፣ ደንብ፣ መመሪያና ውሳኔ እንዲሁም የቃለ ዐዋዲውን ድንጋጌ ሁሉ ተግባራዊ በሚያደርገው በጠቅላይ ቤተ ክህነት እንዲታዩና ውሳኔ እንዲያገኙ ለማድረግ ያላቸውን ሥልጣንና ተግባር የሚጋፋ ነው፡፡
 • በየአህጉረ ስብከቱ ለሚገኙት ለጠቅላላዋ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አባት በመኾን የቤተ ክህነቱን ጠቅላላ አስተዳደር በበላይ ሓላፊነት የሚመሩትን፣ በየአህጉረ ስብከቱ ክልል በመጀመሪያ ደረጃም ይኹን በይግባኝ የሚቀርቡ የሕግና የሥነ ሥርዐት ጉዳዮች በየአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤቶች እንዲታዩ የማድረግ፣ በየአህጉረ ስብከቱ ክልል አዲስ ለሚተከሉ አብያተ ክርስቲያን በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ፈቃድ የመስጠት፣ የመሠረት ድንጋይ የማኖርና ቅዳሴ ቤቱን የመባረክ ሥልጣንና ተግባር ያላቸውን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሚና የሚያሳጣና ትርጉመ ቢስ የሚያደርግ ነው፡፡
 • በአስተዳደር፣ በፍትሕ መንፈሳዊ፣ በአገልግሎትና በምጣኔ ሀብት በኩል በራሷ ሕግና ሥነ ሥርዐት በመመራትና በመደራጀት እንድትሠራ ለማድረግ ታስቦ በዐዋጅ የወጣውን የቃለ ዐዋዲ ደንብ በመተላለፍ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ያልታወቁና ያልታቀፉ፣ በሀገረ ስብከት ወይም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ያልተፈቀዱ ‹‹የካህናት፣ የምእመናን፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች›› ማኅበራትን እንደ አሸን የሚያፈላ፣ ጆቢራዎችንና ሕገ ወጦችን የሚያበረታታ ነው፡፡
 • በአጠቃላይ÷ በካህናትና ምእመናን አንድነት በማእከላዊ አስተዳደር የተደራጀውን የቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ መዋቅር ለሕገ ወጥ ጥቅመኛ ቡድኖችና ግለሰቦች እንዲሁም ለአፅራረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ በማጋለጥየፕሮቴስታንቲዝምን ራስ በቀል ዘይቤ የሚያስፋፋ ነው፡፡

 

ልዩ ትኩረት ከሚያሻቸው የመመሪያው ረቂቅ አናቅጽ ጥቂቶቹ

 

የመመሪያው ስያሜ፡-

 • ‹‹የሃይማኖት ወይም እምነት ተቋማትን ለመመዝገብና የዕድሳት አገልግሎት ለመስጠት የወጣ መመሪያ ቁጥር 1/2005››

አንዳንድ የመመሪያው ትርጓሜዎች፡-

 • ‹‹ተቋም›› ማለት፡- ሰዎች የመረጡትንና የተቀበሉትን ሃይማኖት ወይም እምነት ይዘው በይፋ ለማምለክ፣ ለመከተል፣ ለመተግበር፣ ለማስተማር፣ ለመግለጽ ወይም ለማስፋፋት እንዲያስችላቸው ያደራጁትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማስገኘት ዓላማው ያልኾነ በሚመለከተው አካል ተመዝግቦ ሕጋዊ ሰውነት የተሰጠው የሃይማኖት ወይም እምነት ተቋም ነው፡፡
 • ‹‹መተዳደሪያ ደንብ›› ማለት፡- የሃይማኖት ወይም እምነት ተቋሙ የተቋቋመለትን ወይም ሊያራምደው የሚፈልገውን ዓላማ በተመለከተ፣ ስለአባልነት፣ መብትና ግዴታ፣ ስለ አስተዳደራዊ መዋቅሩና ተግባሩ፣ ስለ ማኅበሩ መዋሐድ፣ ኅብረት መፍጠር፣ ሕጋዊ ሰውነት ማጣት፣ ስለንብረቱ ዕጣ ፈንታ፣ ስለ ደንብ መሻሻልና በአጠቃላይ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚገልጽና የሚወስን ሰነድ ነው፡፡
 • ‹‹ሃይማኖት›› ማለት፡- አማኞች ዋና እና መሠረታዊ ነው ብለው የሚያምኑበትና የተስማሙበት ሲሆን እምነትን ያካተተ ነው፡፡
 • ‹‹ልማት›› ማለት፡- ከሃይማኖታዊ ተግባራት ውጭ በቋሚነት የሚከናወኑ የበጎ አድራጎት ማለት ነው፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ምሥረታ፣ ምዝገባ እና የፈቃድ እድሳት

 • ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም ሕጋዊ ሰውነት የሚያገኘው በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተመዝግቦ የምስክር ወረቀት ሲሰጠው ነው፡፡
 • 50 ሰዎች የሃይማኖት/የእምነት ተቋም መሥርተው ለምዝገባ ማመልከት ይችላሉ
 • በማኅበር፣ ሚኒስትሪ፣ ፈሎሺፕ፣ በአገልግሎትና መሰል ሃይማኖታዊ አደረጃጀት ለመንቀሳቀስ የ15 ሰዎች ማመልከቻ በቂ ነው፡፡
 • የምዝገባ ፈቃዱ በየሦስት ዓመቱ መታደስ አለበት፡፡
 • በሃይማኖት/እምነት ተቋማት መተዳደሪያ ደንብ ዝግጅት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እንዳስፈላጊነቱ መነሻ የሚኾን ሞዴል መተዳደሪያ ደንብ የማዘጋጀት ተግባር አለው !! 

የሃይማኖት/እምነት ተቋማት ግዴታዎችና የተከለከሉ ተግባራት፡-

 • ሃይማኖታዊ ተግባርን ከልማት ተግባር ጋራ ቀላቅሎ መሥራት አይፈቀድም፡፡
 • የሃይማኖት ተቋማት ፀረ – ሰላም፣ አክራሪነትና የጽንፈኝነት እንቅስቃሴዎችን የመከላከል፤ በተከታዮቻቸው ወይም አባሎቻቸው መካከል እና ከሌሎችም ሃይማኖቶችና እምነቶች ጋራ መከባበርና ሰላም እንዲሰፍን የመሥራት ግዴታ አለባቸው፡፡
 • በአገር ውስጥም ይኹን በውጭ አገር ከሚገኙ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐቱን በመቃረን ከሚንቀሳቀሱ ሰዎች ጋራ ማንኛውም ዐይነት ግንኙነት ከማድረግ ወይም በማናቸውም ኹኔታ ከመርዳት ወይም ርዳታ ከመቀበል ራሳቸውንና ተከታዮቻቸውን መከላከል አለባቸው፡፡
 • ከሃይማኖት ጋራ ተያያዥነት ያላቸውን ማስታወቂያዎች፣ ብሮሸሮች፣ መጽሔቶች፣ በራሪ ጽሑፎች በመደበኛ የትምህርት ተቋማት እንዲሁም በማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ተቋማት ግቢ ውስጥ መለጠፍ፣ በመቀስቀሻነት መጠቀምና ማሰራጨት ክልክል ነው፡፡

ሪፖርት፣ ዕድሳት፣ ክትትልና ድጋፍ፣ የማስተካከያ ርምጃ እና ሕጋዊ ሰውነት ማጣት

 • በአንድ የበጀት ዓመት ከብር 500,000 በላይ የሚያንቀሳቅሱ የሃይማኖት/እምነት ተቋማት÷ በሕጋዊ ኦዲተር ተወዳድሮ ባሸነፈ የውጭ ኦዲተር፣ ከብር 500,000 በታች የሚያንቀሳቅሱ በበላይ አካል በተመረጠ የውስጥ ኦዲተር ሒሳባቸውን በየዓመቱ የማስመርመር፣ ለበላይ አካል ቀርቦ የጸደቀውን የኦዲት ሪፖርት አስተያየቶችንና የተሰጡ ውሳኔዎችን ከያዘ ቃለ ጉባኤ ጋራ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡
 • ማንኛውም የሃይማኖት/እምነት ተቋም በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የመረጣቸውን መሪዎችና የሥራ ሓላፊዎች ዝርዝር መረጃ መዝግቦ መያዝና ከዓመታዊ የሥራ ሪፖርት ጋራ ለሚኒስቴሩ ማቅረብ አለበት፡፡
 • ዓመታዊ የሥራ ክንውን ሪፖርት ከሃይማኖታዊ ዓላማ ጋራ የተያያዙ ዋና ዋና ክንውኖችን ያካተተ መኾን ይኖርበታል ! ! !
 • የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከልዩ ልዩ አካላት የሚቀርቡለትን ሪፖርቶች፣ አቤቱታዎችና ጥቆማዎች መነሻ በማድረግ በምሥረታ ላይ ባለ ወይም በተመዘገበ የሃይማኖት ወይም እምነት ተቋም ላይ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ሊያደርግ ይችላል፡፡
 • የሚኒስቴሩን ‹‹ክትትልና ድጋፍ የሚሹ ናቸው›› የተባሉት የትኩረት ጉዳዮች÷ የጥቅም ግጭትና ሌሎች ያለመግባባቶች፣ የገቢ ምንጭ መሠረቱና የሚውልበት ተግባር፣ ከዓላማ ውጭ መንቀሳቀስና መሥራት፣ አስፈላጊ መረጃዎች በወቅቱ አለማቅረብና ሲጠየቁ ምላሽ ያለመስጠት፣ ወቅቱን የጠበቀ የፈቃድ እድሳት ያለማድረግ፣ ሕግን ካለማክበር ጋራ በተያያዘ የሚፈጠሩ ጉዳዮች እንደኾኑ ተመልክቷል፡፡
 • ሚኒስቴሩ በክትትል ድጋፍ በሕግና በልዩ አሠራሮች ግንዛቤ ከመስጠት ጀምሮ እንደ አስፈላጊነቱ የሃይማኖት/እምነት ተቋሙን ምዝገባ በማገድ ወይም ፈቃዱን በመሰረዝ ሕጋዊ ሰውነቱን ሊያሳጣው ወይም በሕግ እንዲጠየቅ ሊያደርገው ይችላል፡፡
 • በሃይማኖት/እምነት ተቋማት አመራርና አባላት ወይም በአባላት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ወይም የቅሬታ ጉዳዮች ለሚኒስቴሩ ከቀረቡ ሚኒስቴሩ ጉዳዩ ለተቋሙ የበላይ አካል ቀርቦ ውሳኔ እንዲያገኝ ያደርጋል፤ ሂደቱን በታዛቢነት ሊከታተል፣ በሁለቱም ወገኖች ስምምነት በዕርቅ እንዲያልቅ፣ ለኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ወይም ለሌሎች የሃይማኖት ተቋማት እንዲያዩላቸው በመላክ ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝ ያደርጋል ! ! 

የመመሪያው የተፈጻሚነት ወሰን፡-

 • መመሪያው ሁለትና ከዚያ በላይ በኾኑ ክልሎች ውስጥ በሚሠሩ ሀገር በቀል የሃይማኖት ወይም የእምነት ተቋማት፣ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ መስተዳድሮች በሚሠሩ የሃይማኖት ወይም እምነት ተቋማት፣ የሚሠሩት በአንድ ክልል ቢኾንም በውጭ አገር ተመሥርተው ኢትዮጵያ ውስጥ ቅርንጫፍ በማቋቋም በሚሠሩ እና ኢትዮጵያ ውስጥ በውጭ ዜጎች ተመዝግበው በሚሠሩ የሃይማኖት ወይም እምነት ተቋማት ላይ ተፈጻሚ ይኾናል፡ 

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ሥልጣን፡-

 • ከምዝገባ፣ ዕድሳትና ተዛማጅ አገልግሎቶች እንዲሁም ሌሎች ተያያዥነት ካላቸው ጉዳዮች ጋራ በተገናኘ ሚኒስቴሩ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ብሎም በጠቅላላው የመመሪያው አፈጻጸም የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር የሚሰጡት ውሳኔ የመጨረሻው ይኾናል፡

የመሸጋገሪያ ድንጋጌ፡-

 • ቀደም ሲል በሌላ አካል ተመዝግበው ሥራ ላይ ያሉ የሃይማኖት ተቋማት መመሪያው ከጸናበት ቀን ጀምሮ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በመመሪያው መሠረት እንቅስቃሴያቸውን ማስተካከል አለባቸው፡፡

source:http://haratewahido.wordpress.com/

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s