ደቀ መዛሙርቱ ተቃውሟቸው በረኀብ አድማ አጠናከሩ

 

  • ፓትርያሪኩ ደቀ መዛሙርቱን ለማነጋገር ፈቃደኛ አይደሉም
  • የረኀብ አድማው የፍትሕ ጥያቄያችን እስኪመለስ ይቀጥላል
  • የመንግሥት አካላት ነን የሚሉ ግለሰቦች ደቀ መዛሙርቱን እያስፈራሩ ነው

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ትላንት ማምሻውን ጀምሮ በረኀብ አድማ ላይ ናቸው፡፡ የረኀብ አድማው ተማሪውንና ሠራተኛውን ፍትሕ ያሳጡት፣ እንደ ግል ቤታቸው በመቁጠር የጥቅም መተሳሰሪያና የንግድ ማእከል አድርገዋል የተባሉት ሓላፊዎች ከቦታቸው እስኪወገዱ ድረስ እንደሚቀጥል ደቀ መዛሙርቱ ገልጸዋል፡፡

ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ባለመብላት ተቃውሟቸውን ለማጠናከር የወሰኑት÷ ያቋረጡትን ትምህርት ለመጀመር ፈቃደኛ ካልኾኑ ብርድ ልብስ፣ አንሶላና መታወቂያ አስረክበው ግቢውን እንዲለቁ የኮሌጁ አስተዳደር ያወጣውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ÷ በትላንትናው ዕለት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩን በአካል አግኝተው ለማነጋገር ያደረጉት ሙከራ ባለመሳካቱ ነው፡፡

 

ሁሉም ደቀ መዛሙርት የዕለቱ ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊት በመንበረ ፓትርያሪክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ተገኝተው የፓትርያሪኩን መምጣት ሲጠባበቁ የቆዩ ቢኾንም ፓትርያሪኩ አለወትሯቸው ሳይመጡ መቅረታቸው ተዘግቧል፡፡ ፓትርያሪኩን በመጠባበቅ ላይ ሳሉም በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር በደቀ መዛሙርቱ ላይ የሚዝቱና ደቀ መዛሙርቱን የሚያስፈራሩ የፖሊስ አባላት መስተዋላቸው ተነግሯል፡፡

ፓትርያሪኩን በጽ/ቤታቸው ተገኝተው ለማነጋገር ባለፈው ሳምንት ዐርብ በንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በኩል ቀጠሮ ተይዞላቸው እንደነበር ያስታወሱት ደቀ መዛሙርቱ÷ በቀጠሮው ቀን ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ ለመግባት ሲሞክሩ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የጥበቃ አባላት ‹‹ዕለቱ የቋሚ ሲኖዶስ የስብሰባ ቀን ነው፤ እናንተን የሚያናግራችኹ የለም፤ ከጀርባችኹ ሌላ ነገር አላችኹ፤›› በሚል መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎቹን ከኮሌጁ አስተዳደር ሓላፊዎች ጋራ በማገናኘት ሁለት ጊዜ ያወያዩት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ሽምግልና መምረጣቸውን ደቀ መዛሙርቱ ገልጸው÷ ከእንግዲህ በየጊዜው እያነሷቸው ሲንከባለሉ የቆዩ ነባር ጥያቄዎች የሚፈቱት በሽምግልና ሳይኾን ተማሪውንና ሠራተኛውን ፍትሕ ያሳጡት፣ ኮሌጁን እንደ ግል ቤታቸው በመቁጠር የጥቅም መተሳሰሪያና የንግድ ማእከል ያደረጉት ሓላፊዎች ከፊታቸው ገለል ሲደረጉ ብቻ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡

ተቃውሟቸው÷ በአንድ ቆርጦ ቀጥል የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎግ እንደተስተጋባው÷ በምርጫው ወቅት ከነበሩ እንቅስቃሴዎች ጋራ ፈጽሞ እንደማይገናኝ ደቀ መዛሙርቱ ገልጸው፣ ጥያቄዎቻቸውን ለሚመለከታቸው የመንበረ ፓትርያሪኩና የመንግሥት አካላት በደብዳቤና በአካል ቀርበው ማሳወቃቸውን፣ እነርሱም ያመኑበትና በተወሰኑ መልኩም አካዳሚያዊ መብቱ እንዲከበርለት ለሚንቀሳቀሰው ተማሪ ድጋፍ ያደረጉበት ኹኔታ መኖሩን አስረድተዋል፡፡

የምግብ ብክለትና አብዛኛው ተማሪ ጤናው የተጓደለ ከመኾኑ የተነሣ ሕክምና በሚከታተሉበት ክሊኒክ ዶክተሮች ‹‹ምንድን ነው የሚመግቧችሁ?›› እስከ መባል መድረሳቸውን፣ የሚሰጠው ትምህርት የመምህራኑ የዝግጅት አቅም የወረደበትና በአንዳንድ ኹኔታዎች በተማሪውና በመምህሩ መካከል ምንም ልዩነት የማይታይበት መኾኑ፣ ተማሪውን ያላማከለና ዕውቀቱን የሚገነባ አለመኾኑ፣ ይህን አስመልክቶ ተማሪው አቤቱታ ሲያቀርብ ‹‹የምትማር ከኾነ ተማር፣ የማትማር ከኾነ አሳየሃለኹ›› እየተባሉ እንደሚባረሩ ከዚህም አልፎ በውጤት አሰጣጥ አድልዎ የተደረገባቸውና ውጤታቸው እንዲመረመር የሚጠይቁ ተማሪዎችን በቡጢ የሚማቱ መምህራን መኖራቸው፣ የበላይ ሓላፊው ቢሮ ማንኛውንም የተማሪዎች ጥያቄ የማይቀበልና ተማሪዎችን የሚያሸማቅቅ መኾኑ፣ የቤተ መጻሕፍቱ ማመሳከሪያ መጻሕፍት የተገነጣጠሉና ኅትመታቸው የቆዩ መኾናቸው፣ ቤተ መጻሕፍቱ የሚገኝበት ቦታ ኮሌጁ በወር በብር 13,000 ካከራየው ካፊቴሪያ ማዕድቤት አጠገብ የሚገኝና ለአደጋ የተጋለጠ መኾኑ ደቀ መዛሙርቱ በተደጋጋሚ ከሚያነሷቸውና መፍትሔ ካጡት ነባር ጥያቄዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

እኒህን ችግሮች ለማስተካከል የሚያስፈልገው በስም የተጠቀሱትን ሁለት የኮሌጁን ሓላፊዎች ከቦታቸው ማንሣትና በተገቢው ሰው መተካት መኾኑን ያመለከቱት ደቀ መዛሙርቱ÷ ጥያቄያቸውን ከፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ጋራ በማያያዝ ለሚዝቱባቸውና ለሚያስፈሯሯቸው የመንግሥት አካላት ነን ባይ ኀይሎች ጫና እንደማይንበረከኩ ገልጸዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ የኮሌጁ አስተዳደር እስከ ትላንት 6፡00 ሰዓት ትምህርት እንዲጀምሩ፣ የማይጀምሩ ከኾነ እስከ ቀኑ 11፡00 ሰዓት ድረስ ንብረት አስረክበው እንዲወጡ ማዘዙን ጠቅሰው፣ ከዚህ በኋላ ምግብ ባለመብላት ያጠናከሩትን ተቃውሞ ቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ እስከሚሰጣቸው ድረስ ለመቀጠል የጋራ አቋም መያዛቸውን ተናግረዋል፡:

የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s