የደብረ ምጥማቅ መግባቢያ

click here for pdf

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥታዊ ያልሆነች ትልቋ ተቋም ናት፡፡ በሕዝቡ ሃይማታኖዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ታሪካዊ ጉዞ ውስጥ የማይተካና ወሳኝ የሆነ ሚናም አላት፡፡ ዕድገቷ ለሀገሪቱ ዕድገት፣ ሥልጣኔዋ ለሀገሪቱ ሥልጣኔ፣ አሠራርዋ ለሀገሪቱ አሠራር፣ የችግር አፈታቷም ለሀገሪቱ የችግር አፈታት ወሳኝ ነው፡፡
በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግሮች ለመፍታትና አንዲት፣ ጠንካራ፣ በአሠራርዋ ዘመናዊ፣ በእምነቷ ጥንታዊ፣ በሀገሪቱ ጉዞ ውስጥ ተደማጭና ወሳኝ የሆነ ሚና ያላት፣ ሌሎች ችግሮቻችንን በመፍታት ረገድ ሀገራዊ መንፈሳዊና ተልእኮዋን የምትወጣ ቤተ ክርስቲያን እንድትሆን በማድረጉ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ይመለከተናል፡፡
በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከገጠሟት ፈተናዎች አንዱ የመለያየት ዕጣ ፈንታ ነው፡፡ ይህ ዕጣ በተለይም በሀገር ቤትና በውጭ በሚባል ሲኖዶስ፣ በማይግባቡና በማይቀራረቡ አባቶች እነርሱም በተከተሉት ሁለት ዓይነት የችግር አፈታት ምክንያት የተከሰተ ነው፡፡
ይህንን ችግር እንፈታው ዘንድ ከተፈጠሩልን መልካም ዕድሎች መካከል አንዱ ላይ እንገኛለን፡፡ አባቶችም፣ ምእመናንም፣ ሀገር ወዳዶችም ይህንኑ እየጠየቁና እያሳሰቡ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ሁላችንም ልናየው የምንመኘውን የቤተ ክርስቲያን አንድነት ሊያመጡ ከሚችሉት መንገዶች አንዱ የሆነው ‹‹ የደብረ ምጥማቅ መግባቢያ›› የተሰኘው መግባቢያ ነው›፡፡
ደብረ ምጥማቅ በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ተጉለት ውስጥ የምትገኝ ቦታ ናት፡፡ በ14 ኛው መክዘ በንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት የመለያየት ፈተና ተጋርጦባት የነበረችውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አንድ ለማድረግ ሲባል ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ጉባኤ የተደረገባትና አንድነቱም የተገኘባት ቦታ ናት፡፡
ከ13ኛው መክዘ ጀምሮ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን እንድነት የፈተነ አንድ ጥያቄ ነበር፡፡ የሰንበት አከባበር ጉዳይ፡፡ በአንድ በኩል መከበር ያለባት ሰንበተ ክርስቲያን ብቻ ናት በሚሉትና በደብረ ሊባኖስና በሐይቅ እስጢፋኖስ አባቶች በሚመሩት፤ በሌላ በኩል ደግሞ መከበር ያለባቸው ቀዳሚትም የክርስቲያን ሰንበትም ናቸው በሚሉት በአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ደቀ መዛሙርትና በደብረ ብሥራት ዜና ማርቆስ (ሰሜን ሸዋ) በሚመሩት አባቶች መካከል የሀሳብ ልዩነት ተፈጥሮ ነበር፡፡
ይህ የሃሳብ ልዩነት ወደ አለመግባባት አምርቶ የሁለት ሰንበት ሃሳብ አስተማሪ የነበሩት አቡነ ኤዎስጣቴዎስ መጀመርያ ወደ እስክንድርያ፣ በኋላም ወደ አርመን(ቆጵሮስ) ሄዱ፡፡ በዚያውም በስደት ዐረፉ፡፡ የእርሳቸው ደቀ መዛሙርት የሚገኙባቸው በኋላም ኤርትራ በሚገኘው ደብረ ቢዘን ይመሩ የነበሩት ገዳማትና አድባራትም በአብዛኛው በስተዳደር ጉዳዮች ከመሐል ሀገር አብያተ ክርስቲያናት እየተለዩ መጡ፡፡ በተለይም ደግሞ ዐፄ ዳዊት ችግሩን ለመፍታት በጠሩት የሐይቅ እስጢፋኖስ ጉባኤ ላይ የተገኙትን የደብረ ቢዘኑን አቡነ ፊልጶስን በዚያው በሐይቅ በግዞት እንዲቀመጡ ማድረጋቸው ችግሩን አባባሰው፡፡ በሰሜን ትግራይና በኤርትራ የነበሩ ገዳማትና አድባራትም ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ከመካከለኛው ሕዝብና ቤተ ክህነት ተለያዩ፡፡
ችግሩ የተፈታው ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ወደ ሥልጣን ሲመጣ እና ሁለቱም አባቶች የተሳተፉበት ጉባኤ በደብረ ምጥማቅ በ1442ዓም በተደረገ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ የደብረ ምጥማቅ ጉባኤ ሁለቱም ወገኖች ተገኝተው በችግሩ መፍትሔ ላይ ተወያዩ፡፡ መለያየታቸውን ለማስወገድ ተስማሙ፡፡ ሁለቱም ሰንበቶች እንዲከበሩ፤ ነገር ግን የቀዳሚት ሰንበት አከባበር እንደ አይሁድ የሰንበት አከባበር እንዳይሆን ከመግባባት ላይ ደረሱ፡፡
ይህ መግባባት የመለያየት አደጋ ተፈጥሮባት የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ወደ አንድነት በማምጣትና መለያየቱም መልክዐ ምድራዊ አቅጣጫ እንዳይከተል በማድረግ ታላቅ ሚናን ተጫውቷል፡፡ ለዚህ ነው ይህ ለዛሬዋ ቤተ ክርስቲያናችን አንድነት የቀረበው መግባቢያ በዚሁ ስም የተሰየመው፡፡ ከራሳችን ልምድ እንድንማር ተብሎ፡፡
የደብረ ምጥማቅ መግባቢያ
1.     ባለፈው ላይ መነጋገር ማቆም፡- በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የሚደረገውን የአንድነት ውይይትም ሆነ፣ እኛ ሌሎች አካላት የምናደርገውን አስተዋጽዖ የሠመረ ለማድረግ ውይይቱ በቀጣይ የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ እንጂ በትናንቱ ላይ እንዳይመሠረት ማድረግ፡፡ ትናነት ማን ነበር ጥፋተኛ? እገሌ ለምን እንደዚህ አደረገ? ለምን እንደዚህ አላደረገም? እያልን መከራከራችንን ብናቆየው፡፡ ምክንያቱም ትናነትን መቀየር አይቻልም፡፡ ሆኗል፡፡ ልንሰጠው የምንችለው ትርጉም ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ያከራክራል፤ ከዚያም አልፎ ያጨቃጭቃል እንጂ መፍትሔ አያመጣም፡፡ አንዱ ከሳሽ ሌላው ተከሳሽ፤ አንዱ ወቃሽ ሌላው ተወቃሽ፣ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ እየሆነ ግብግብ ከመፍጠር ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ ስለዚህ ነገ አንድነቱ ሲመሠረት ገለልተኛ የሆነ አካል አቋቁመው ሁለቱም አካላት ትምህርት እንዲወስዱበት የትናነቱ ወደፊት በባለሞያ ይጠና፡፡ አንድ ሆነንም ማን እንደነበርን ያኔ እናየዋለን፤ እንሰማዋለንም፡፡ አሁን ግን በምናደርጋቸው ውይይቶች የትናንቱን ትተን በነገው መፍትሔ ላይ እንመሥረት፤ ነገ በእጃችን ላይ ስለሆነ፤ ትናንት ግን አምልጦናል፡፡
2.   ሁሉን ዐቀፍ ይቅርታ፡- ለተፈጠረው ችግር የተወሰኑ ግለሰቦችን፣ አካላትን ወይም የታሪክ አጋጣሚዎችን ብቻ እየኮነንና እያወገዝን ከምንጨቃጨቅ፤ ሁሉም ራሱን ነጻ ለማድረግም ከሚረባረብ   ‹‹የበደልነው ሁላችንም ነን፤ የተበደለውም እግዚአብሔር ብቻ ነው›› ብለን አምነን ሁላችንም ሁላችንን እና ሁላችንም እግዚአብሔርን ይቅርታ ብንጠይቅ፡፡ ይህም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በአንድ በታወቀ ዕለት ከሁለቱም ወገን በሚወከሉ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መነኮሳት፣ ምእመናንና አገልጋዮች አማካይነት ለሕዝብ ግልጥ ሆኖ ቢከናወን፡፡ ይህ ሁኔታ በአንድ በኩል ክርስትናችን የሚያዘን ነውና የእግዚአብሔርን ረዳትነት ያስገኝልናል፤ በሌላም በኩል አንዱ በሌላው ላይ ጣት መጠቆሙን፣ የክስ ፋይልም መተንተኑን አቁሞ ነገሩን በጋራ ለመዝጋት ያስችለናል፡፡
3.   ውግዘቱን ማንሣት፡- በሁለቱም አካላት የተላለፉትን ውግዘቶች ከይቅርታው በኋላ አከታትሎ በሁለቱም አካላት አማካይነት እንዲነሡ ማድረግ፡፡
4.ሁለቱም አካላት ችግሩን ከሚያባብሱ ተግባራትና አዝማሚያዎች መቆጠብ፡-እያንዳንዱ ወገን የሚያከናውነው ነገር ሰላሙንና አንድነቱን የሚያጠናክር እንጂ ችግሩን የሚያባብስ እንዳይሆን መጠንቀቅ፡፡ ሁለቱም አካላት ይህንን የሚከታተል የጋራ ኮሚቴ አቋቁመው እነዚህን ተግባራትና አዝማሚያዎች መከታተልና እንዲታረሙ ማድረግ፡፡ ግለሰቦችንና ቡድኖችንም መገሠጽ፤
5.   የጋራ የእርቅ ኮሚቴ መመሥረት፡- እስካሁን ውይይቶቹ በሦስተኛ አካል በኩል የሚደረጉ ናቸው፡፡ ዕርቁ ከተፈጸመና ውግዘቱ ከተነሣ በኋላ የጋራ የሊቃነ ጳጳሳትና የሊቃውንት ኮሚቴ ማቋቋምና ቀጣዩ ሂደት ምን እንዴት መደረግ እንዳለበት አንድ ሆኖ ሰነድ ማዘጋጀት፡፡ በዚህ ሰነድም
·     የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሁኔታ
·  በውጭ ሀገር ያሉ አባቶች ወደ ሀገር ለመግባት የሚችሉበት ሁኔታ
·  በልዩነቱ ዘመን የተፈጠሩ ሕጋዊ፣ ተቋማዊና አስተዳደራዊ ልዩነቶች ስለሚጣጣሙበት ሁኔታ
·   የሀገረ ስብከት ድልድል
·   አንድ የሚያደርግ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ
·   ከሰላሙና ከአንድነቱ ሂደት የሚያፈነግጡትን በተመለከተ
· ሌሎች ጉዳዮችን የሚመለከቱ ነገሮችን በዝርዘርና ከነ መፍትሔያቸው አንድ ሆኖ በድርድር መንፈስ ሳይሆን የጋራ መፍትሔ በመስጠት መንፈስ ማከናወንና በሁለቱም አካላት አስጸድቆ የጋራ ሰነድ ማድረግ
6.  የ2006ን የጥቅምት ሲኖዶስ በአዲስ አበባ ማድረግ፡- በ2005 ችግሮቹን ሁሉ ፈትቶ የ2006ን የጥቅምት ሲኖዶስ ጉባኤ ሁሉም አባቶች በሚገኙበት በአዲስ አበባ ማከናወን፡፡ በዚህ ቀን ሕዝብ የሚሳተፍበት የአንድነት በዓል ማዘጋጀትና ከሁለቱም ወገን በሚወከሉ አባቶች ለሕዝቡ የሰላምና የአንድነት ትምህርት እንዲሰጥ ማድረግ፡፡ በዚህ የጥቅምት ጉባኤም የመለያየቱን ዘመን በአንድነት ጉባኤ መዝጋት፡፡
ነገሩ እንደሚጻፈው ያህል ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን ላመነ ሁሉም ይቻላል ለምንል ክርስቲያኖች ዓለም ከዚህ በላይ ይጠብቅብናል፡፡ ማየት ያለብን የየራሳችንን አመለካከት አይደለም፤ የየራሳችንንም ጥቅም አይደለም፤ የየራሳችንንም በጎ ሃሳብ አይደልም፡፡ ማየት ያለብን ታላቋን ሥዕል ቤተ ክርስቲያንን ነው፡፡ አንዳንዱን ነገር እየተውን፤ አንዳንዱን ነገር እያሳለፍን፤ አንዳንዱን ነገር እየተሸነፍን፤ አንዳንዱንም ነገር እየናቅን መሻገር አለብን፡፡ ወደሚያግባባን እንጂ ወደሚለየን፤ ወደሚያስታርቀን እንጂ ወደሚያኳርፈን አንጓዝ፡፡ አንድ ትውልድ በመለያየቱ ግንብ ውስጥ ተወልዶ አድጎ፣ ለወግ ለማዕረግ በቃ፡፡ አይበቃንም? ለመሆኑ ስንት ትውልድ ማለፍ አለበት?
አሁን ሁላችንም ከጸሎት ጋር ከዚህ የተሻሉ ሃሳቦችንም በማምጣት፤ ይህንንም በማዳበር ግፊትና ጥረት እናድርግ፡፡
የሰላም አምላክ ይርዳን፡፡ አሜን፡፡
Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s