ዜናዎች

የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ምእመናን አቡነ ማርቆስ ያደረሱትን አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ በደል ለጠቅላይ ቤተክህነት አቀረቡ

 ማርቆስ
 • መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር አዲስ አበባ የሚኖሩ የደብረወርቅ ተወላጆችን “አቡነ ማርቆስ ደብረወርቅ ላይ ልማት በመጀመራቸው ተቃውመው ነው የመጡት” በማለት በርካታ ምእመናን በተሳሳተ አጀንዳ ቢያሰባስብም፣ ጉዳዩ ሃይማኖታዊ መሆኑን ስለተረዱ ይቅርታ ጠይቀው ተመልሰዋል።
 • አቡነ ማርቆስ የቀረበባቸው ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ በደል ባሻገር በልማድ “ቅባት”ና ተዋህዶ በመባል ተከፋፍሎ የሚኖሩት የሀገረ ስብከቱ ምእመናን ርስበርሳቸው የሚያጋጩ ሥራዎች በመስራት ላይ መሆናቸው ጠቅላይ ቤተክህነትንና መንግስትን አሳስቧል።
 • አቡነ ማርቆስ የገዟቸው ቤቶች (በአዲስ አበባ ሁለት፣ በግንደ ወይንና ሻሸመኔ) የሃብት ምንጫቸው የቤክህነቱን ትኩረት ስቧል።
 •  ምዕመኑ ከ116 ገጽ የድጋፍ ፊርማ ጋር አቤቱታውን አብሮ አቅርቧል
 • ጠቅላይ ቤተክህነቱ አጣሪ ኮሜቴ ወደ አገረስብከቱ ይልካል።
ክፍል  ሁለት  
(አንድ አድርገን ታህሳስ 2 2005ዓ.ም) አቡነ ማርቆስ በሃገረስብቱ ላይ ያደረሱትን በደል ባለፈው በክፍል አንድ(ክፍል አንድ ለማንበብ ይህን የጫኑ ) ጽሑፍ ማስነበባችን ይታወቃል። ይህን ተከትሎ ርቱዓነ ሃይማኖት የሆኑ የሃገረስብከቱ ምዕመናን በቤተክረስቲያኗ መዋቅር የስልጣን ተዋረድ መሰረት ለጠቅላይ ቤተክህነቱን የአስተዳደር ዘርፍ ምክትል ሥራአስኪያጁን አቶ ተስፋዬ ውብሸት ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ከም/ሥራ አስኪያጁ ጋር የምእመናን ተወካዮች ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ምንጮቻችን ዘግበዋል። በውይይቱ ወቅት ም/ሥራ አስኪያጁ “ የቤተክርስቲያንን ማንነትና ክብር የሚያስጠብቅ እስከሆነ ድረስ ችግሩን የማንፈታበት ምክንያት የለም” ማለታቸው ተሰምቷል። በቀጣይ አጣሪ ኮሚቴ ወደ ሀገረስብከቱ እንደሚላክና ያሉትን ማስረጃዎች ለአጣሪ ኮሚቴ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸበር የደብረወርቅ ተወላጅ የሆኑ በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ በተለይ ደግሞ በታላቋ በደብረ ወርቅ ማርያም ገዳም “ውሉደ አርከ ሥሉስ ዘደብረወርቅ የአብነት ትምህርት ቤቶች ማጠናከሪያ ማኅበር” አባላትን በተሳሳተ አጀንዳ “ የመጡት እናንተ የጀመራችሁትን የልማት ሥራ ለመቃወም እና አባ ማርቆስ ለደብረወርቅ ትኩረት ለምን ሰጡ?” ብለው ነው በሚል ሸውከኛነቱ በሚያሳጣ መልኩ ከምእመናን ተወካዮች ጋር ለማጋጨት የሞከረ ቢሆንም በሁለቱም በኩል ባሉ በሳል ምእመናን አማካኝነት ውይይት በማድረግ ጉዳዩ የጋራቸው መሆኑን ተግባብተዋል። የተወሰኑትም “በሃገር ልጅነት ብቻ” እና በተሳሰተ አጀንዳ አቡነ ማርቆስን እንዲደግፉ በመጠራታቸው አዝነው ወደ ስራ ቦታቸው መመለሳቸውና የቀሩት ደግሞ ጥያቄውን ከምእመናን ተወካዮች ጋር ማቅረባቸው ታውቋል። ይህ መንፈሳዊ ማኅበር ቀናዒ አባት ካገኘ በደብረወርቅ ብሎም በሃገረስብከቱ የሚገኙ አብነት ትምህርት ቤቶች ችግር መቅረፍ እንደሚችል ይታመናል።
 11
 ውሉደ አርከ ሥሉስ ዘደብረወርቅ የአብነት ትምህርት ቤቶች ማጠናከሪያ ማኅበር ካሰሩአቸው 19የተማሪዎች ቤቶች መካከል
ከስብከተ ወንጌል መመሪያ ሃላፊነቱ በተጠረጠረበት ኑፋቄ የተወገደው አእመረ አሸብር በ1992 ዓ.ም በኑፋቄው ቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖና ሰጥቶት ከመቀሌ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ተባሮ እንደነበርና የሃገረስብከቱ ሊቀጳጳስ የነበሩት አቡነ ዘካርያስ “ቀኖናውን ፈጽሟል” የሚል ደብዳቤ ለኮሌጁ በመጻፍ ያቋረጠውን ትምህርት ተመልሶ የጨረሰ ሲሆን በሃገረ ስብከቱ ታዋቂ የቅኔ መምህር የነበሩትን መርጌታ አሥራትንና 24 ደቀመዛሙርቶቻቸውን እንዲሁም በቅዱስ ማርቆስ ይማሩ የነበሩ 12 ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ወደ መናፍቃን ጎራ እንዲቀላቀሉ አድርጎአል። በአካባቢው ፕሮቴስታንቶች ዘንድ “የወንጌል ወታደሩ” በመባል ይታወቃል። በአሁኑ ሰዓት መናፍቅነቱን አጋጣዊዎችን በመጠቀም በግልጥም በስውር እያራመደ እንደሚገኝ ማስረጃዎች ያሳያሉ።
 212
                                        መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር
ምእመናኑ ያቀረቡት አቤቱታ ከጠቅላይ ቤተክህነት ምንጮቻችን ደርሶናል እንደሚከተለው እናቀርበዋልን
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ቀን፡- ኅዳር30/2005 ዓ.ም
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
አዲስ አበባ 
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣
ከሁሉም በፊት የሀገረ ስብከቱን ምእመናን አቤቱታ ለመስማት በመፍቀዳችሁ በእግዚአብሔር ስም እያመሰገንን እኛ በሀገረ ስብከቱ በተለይም በደብረ ማርቆስ ከተማና አካባቢው የምንኖር የቤተክርስቲያን ልጆች በሀገረ ስብከቱ የተከሰቱትንና እየተከሰቱ ያሉትን ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ለመፍታት ከብፁዕነታቸው ጋር የመንግስት ከፍተኛ የአመራር አካላትንም በመጨመር ተደጋጋሚ ውይይት ለማድረግ የሞከርን ቢሆንም ብፁዕነታቸው በሚያሳዩት አባታዊ ያልሆኑ ንግግሮች ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ እኛም የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ተሰባስበን በመወያየት የቤተክርስቲያኒቱን እሴት የሚያንኳስሱ ክንዋኔዎች፤አሠራሮችና ሁኔታዎች ከዕለት ዕለት እየበዙ በመምጣታቸው ጉዳዩን ለቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አካል ለቅዱስ ሲኖድስ ሰላማዊና ተቋማዊ መዋቅሩን በጠበቀ መልኩ ይኸው ዛሬ ለማቅረብ ተገደናል፡፡
ምክንያቱም፡-
í) በሀገረ ስብከታችን እየተከሰቱ ያሉ አስተዳደራዊና ሃይማኖታዊ ችግሮችን ከምንጩ ለማስረዳት፤
î) አሁን የተከሰቱትና እየተከሰቱ ያሉት ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ምንም መፍትሔ ሳይበጅላቸው በዚህ አካሄድ ከቀጠሉ ለሀገረ ስብከታችን እና ለመላ ቤተክርስቲያናችን ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ ከወዲሁ መፍትሔ እንዲፈለግበት፤
ï) ሀገረ ስብከታችን ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው “ከቅባት” ጋር የተገናኙ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት አባቶቻችንና መላ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ልዩ ትኩረት እንዲሠጡት ለማስገንዘብ ሲሆን ብፁዕነታቸው አቡነ ማርቆስም በተደጋጋሚ ራሳቸውን ከሁሉም የተለዩ ፣የማይገኙ ፣ የማይተኩ ፣ እሳቸው ያሉትን የማይቀበል ያልዳነና ያልገባው መሆኑን በመግለጽ ካህናቱን በመሳደብ፣ ምእመኑን ወንጌል ያልገባው በደብተራ የተተበተበ እና ሌሎች የንቀት፣ የስድብ እና የእርግማን ንግግሮችን በመናገር የበደሉን በመሆኑ ለችግሮች መፍትሔ ለማፈላለግ እንጂ አቤቱታችን ከጭፍን ጥላቻና ነቀፌታ የነፃ ፍጹም ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ መፍትሄን በመሻት ነው፡፡
        íኛ. አስተዳደራዊ ችግሮች
ብፁዕነታቸው አቡነ ማርቆስ ወደ ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት እንደመጡ ብዙ ጉዳዮችን በትችት ሕዝቡንም በንቀት የተመለከቱ ሲሆን በመጡ በ3ኛ ወራቸው ጀምረው፡-
í)  ከ41 በላይ ሹም ሽርና እገዳ ያካሄዱ ሲሆን አብዛኛዎቹ ሹም ሽሮችና እገዳዎች ሕገ ቤተክርስቲያንን /ቃለ አዋዲውን/ ያልተከተሉ፤ተቋማዊ መዋቅሩን የጣሱ ይገኙባቸዋል፡፡
î) ቅድስት ቤተክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ በቃለ ዓዋዲው መሠረት የተቋቋሙትን ሰ/ት/ቤቶችን “ወንበዴዎች፤ሌቦችና አሸባሪዎች” በማለት በሕዝብ ፊት ተሳድበው ለሰዳቢ ሠጥተዋል፡፡
ï በንጹሐን ምእመናን ላይ ሰብአዊ ክብርንና ነፃነትን የሚጋፋ የስድብ፤ንቀትና እርግማን አካሄደዋል፡፡
ð ) ብፁዕነታቸው ከሦስት በላይ መኖሪያ ቤቶች ያሏቸው ሲሆን ከእነዚህም መካከል ተወልደው ባደጉበት፣ በተማሩበትና ባስተማሩበት ጉንደወይን ከተማ /በ2004 ዓ.ም የተገዛ/ እና አዲስ አበባ / በ2000 ዓ.ም የተገዛ/ ያላቸው ሲሆን ከአዲስ አበባው መኖሪያ ቤት የግንባታ ውል ክፍያ ጋር በተያያዘ በብፁዕነታቸው በብፁዕ አቡነ ማርቆስ ላይ የተፈጸመው ክስና እስራት በሀገረ ስብከታችን ያሉትን ምእመናንን አንገት ሰብሯል፤ አዋርዷል፡፡ በዚህም ወቅት በሀገረ ስብከታችን አስተዳደር ውስጥ በሂሳብ ሹም፣ ገንዘብ ያዥና መዝገብ ቤት መካከል  ሦስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአንድ ቀን የተደረጉ ለውጦችና ሰዎቹ ለብፁዕነታቸው ካላቸው ዝምድናና አካሄድ አንጻር ነገሩን ለሀገረ ስብከቱ ምእመናን ከጥቂት ዓመታት በፊት በብፁዕነታቸው አቡነ ዘካርያስ ከተፈጸመብን በደል አንጻር እንቅስቃሴውን እንቆቅልሽ  አድርጎብናል፡፡
îኛ. ሃይማኖታዊ ችግሮች
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ወደ ሀገረ ስብከታችን ከመጡበት ከኅዳር 2004 ዓ.ም ጀምሮ በካህናት፤በዲያቆናትና በሌሎች የቤተክርስቲያኒቱ ምእመናን ዘንድ ያልተለመዱ፤እንግዳ ክንዋኔዎች እየተስተዋሉ ሲሆን ክንዋኔዎቹና አሠራሮቹም ምእመናንን ግራ ያጋቡ፤ለመናፍቃንም በር የከፈቱና የሚከፍቱ ናቸው፡፡
ከእነዚህም መካከል ፡-
1 ) ብፁዕነታቸው አቡነ ማርቆስ ከመጡ ከሁለት ወራት በኋላ ጀምሮ የቅድስት ቤተክርስቲያናችን ቅዱሳን አበው ለመናፍቃን መልስ የሰጡበትና ለአማኞች ያስተማሩበት ሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ‹‹እኔ ልማታዊ ነኝ ጊዜውን በአግባቡ መጠቀም አለብን›› በሚል ተገቢ ያልሆነ ምክንያት ከቅዳሴ በኋላ እንዳይነበብ ተደርጓል፡፡
2) በአንዳንድ አድባራትና ገዳማት በውል በታወቀ ምክንያት የቅዳሴ ጸሎት ሰዓቱ ቢቀየርም በፍትሐ ነገስት አንቀጽ 12 ላይ ‹‹ሕዝቡ ሳይሰበሰቡ የቅዳሴውን ጸሎት አይጀምሩ›› የሚለውን በመተው በሀገረ ስብከታችን ለብዙ ዘመናት ምቹ ከሆነው ንጋት የ12፡00 ሰዓት የቅዳሴው ጸሎት ያለ ምንም ተጨባጭ ምክንያት ‹‹ሰዓቱን ለወንጌል መጠቀም አለብን›› በሚል ምክንያት ወደ 11፡00 ሰዓት እንዲሆን ተደርጓል፡፡በዚህም እናቶች፤እህቶች፤ሕጻናትና አረጋዊያን ሌሊት 10፡00 ሰዓት ከቤታቸው እንዲወጡ በመገደዳቸው መቸገራቸውን፤መማረራቸውንና በቅዳሴ ሰዓትም የምእመኑ ቁጥር መቀነሱን እንገልጻለን፡፡
 3)  በክብር ለቡራኬ በእጃችን በማድረግ እንቀበለው የነበረውን የቅዳሴ ጸበል ያለ ምንም ምክንያትና ጥቅም ብፁዕነታቸው በጆግ በማደረግ በጅምላ ምዕመናንን መርጨት በማዘውተራቸው ምእመናንም ሲጠይቋቸው‹‹እንግዲያውስ አረቄና ጠላ ልርጫችሁ?›› በማለት የተዘባበቱና የመለሱ ሲሆን ነገና ከነገ ወዲያ ይህ አካሄድ ወደ ቅዱስ ቁርባኑ የማይሄድበት ምንም ተጨባጭ ምክንያት እንደማይኖር እንገልጻለን፡፡
 4) በቅዳሴ ጸሎት ጊዜ ታቦተ መንበሩን ለምእመናን ግልጥ ሆኖ እንዲታይ በማስገደድ (ካህናቱ ሥጋውና ደሙን ሲፈትቱ እንዲታይ በማድረግ) በአካባቢው ሽማግሌዎች አበባል ‹‹የኢትዮጵያ ሙሽራ ዛሬ ተገለጠ ክፉ ቀን መጣ›› እስኪባል ድረስ ብዙ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም በቤተክርስቲያናችን ያልተለመደ የጸሎተ ቅዳሴ ሥርዓት እንድንከተል እየተገደድን እንገኛለን፡፡
5) በቅድስት ቤተክርስቲያናችን የሥርዓት መጽሐፍት በሆነው በፍትሐ ነገስት መሠረት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጾሙን ወራት በሚታሰብበት በጾመ ኢየሱስ ወይም ዐቢይ ጾም በአርምሞ፤በጾምና በጸሎት፤በንስሐና ቅዱስ ቁርባን፤በሱባኤ የጌታን ሕማማተ መስቀል እያሰቡ ማዘን፤ማልቀስ የሚገባ በመሆኑ ከበሮ የማይመታ የማይጨበጨብ ቢሆንም ብፁዕነታቸው ይህንን ሥርዓት በመተው ምእመናን “አልለመድንም ከበሮ አንመታም አናጨበጭብም” ቢሉም ‹‹እኔ ሊቀ ጳጳሱ ተቀምጬ፤እኔ ፊታችሁ እያለሁ›› በማለት በደ/ማርቆስ ከተማ በሚገኘው ጽርሐ ጽዮን አብማ ማርያም ቤተክርስቲያን በተደረገ ጉባኤ ምእመኑ ሳይፈልግ በማስገደድ ከበሮ አስመትተዋል፤ አስጨብጭበዋል፡፡
 6)  ካህናት ምእመናንን በተለይም የንስሐ ልጆቻቸውን በቅርብ መከታተል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ መሰረት ካህናቱ በየንስሐ ልጆቻቸው ቤት በመዘዋወር ቡራኬ ይሰጣሉ፡፡ ብፁዕነታቸው ግን የሀገረ ስብከቱን ካህናት ክብርን በሚነካ መልኩና በጸበሉ ፈዋሽነት አለማመንን በሚያሳይ አነጋገር ‹‹ውኃ ግድግዳ ላይ ከመርጨት በቀር ወንጌል የማያውቁ›› በማለት ተሳድበዋል፡፡ ጸበል ውኃ ብቻ ነውን? ካህናቱስ አይባርኩትምን? እርሱስ መጻጉዕ የተፈወሰበት ወንጌል አይሆንም? ካህናቱስ ሌላ አያውቁምን?
7) በፍትሐ ነገስት አንቀጽ 14 ላይ በተገለጸው መሠረት ሴት በወር አበባ(በወርኃ ጽጌ) ወቅትና አራስ ስትሆን ቤተክርስቲያን መግባትን የሚከለከል እንደሆነ ቢታወቅም ብፁዕነታቸው መግባት እንደሚችሉ የፈቀዱ ሲሆን እርሳቸው በተገኙባቸው ጉባኤያት ላይ ‹‹እኔ አባታችሁ እያዘዝሁ፣እኔ ፈቅጄ፣ እኔ የቤተክርስቲያኒቱ ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያው እያለሁ›› በማለት እንዲገቡ በማስገደዳቸው የተወሰኑት እናቶችና እህቶች ትዛዛቸውን አክብረው ሲገቡ ቀሪዎቹ ለቤተክርስቲያን ክብር ሲሉ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ማየት የተለመደ ትርኢት ሆኗል፡፡
8)  ብፁዕነታቸው ከላይ በተራ ቁጥር ሁለት ከተጠቀሰው የቅዳሴ ጸሎት  ሰዓቱን እንዲሻሻል ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ መውጣት እንጂ መግባት ይቻላል በማለት አባቶቻችንና ወላጆቻችን ያላስተማሩንን የማናውቀውን ሥርዓት እንድንከተል እየተገደድን መሆናችንን እንገልጻለን፡፡
9)  ብፁዕነታቸው ነገረ ቅዱሳንን በተመለከተ ግራ የሚያጋባ አቋም ያላቸው ሲሆን የሀገረ ስብከቱ ሰባኪያነ ወንጌልን በመንበረ ጵጵስና ሰብስበው ‹‹ክርስቶስን ስበኩ እንጂ አቡሀይ እሙሀይ አትበሉ›› በማለት ስለ ቅዱሳን ያላቸውን አመለካከት ተናግረዋል፡፡
 በአጠቃላይ በሀገረ ስብከታችን ብፅዕነታቸው ያደረሱብን ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ በደል እኝህ ብቻ ሳይሆኑ የተጠቀሱት ማስረጃ ማቅረብ የሚቻልባቸው ሲሆኑ በዚህ ጹሑፍ ቢቀርቡ የቤተክርስቲያንና የአባቶቻችንን ክብር የሚያስደፈሩ በመሆናቸው ያላቀረብናቸው ሲሆን እኛ በምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የምንገኝ የቅድስት ቤተክርስቲያን ልጆች ከጥቂት ዓመታት በፊት በብፁዕነታቸው አቡነ ዘካርያስ የደረሰብን በደል ከልባችን ሳይሽር ከኃሊናችን ሳይወጣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለችግራችን መፍትሄ ለመፈለግና ምእመናንን ለመካስ ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው በብፁዕነታቸው መቀጠል ሲገባውና የደረሰብንን በደል መካስ ሲገባቸው ድጋሜ ዘርፈ ብዙና መሰረታዊ ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ ችግሮች በመከሰታቸው ምክንያት ይህን ችግር ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አባቶቻችንና ለመላ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ጉዳዩን ለመግለጽ የተገደድን ሲሆን አስፈላጊውን ተቋማዊ መዋቅር ተከትለን ችግሩን ለመፍታት ጥረት ብናደርግም ባለመሳካቱና ምላሽ ባለማግኘታችን መሆኑን እየገለጽን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አባቶቻችን ይህን ጉዳይ በጥልቀትና በስፋት ተመልክተው መፍትሔ እንዲሰጡን ከዚህ ሸኝ ደብዳቤ ጋር ባያያዝነው 116 ገጽ የድጋፍ ፊርማ እየገለጽን እኛ የሀገረ ስብከቱ ምእመናን በቅዱስ እግዚአብሔርና  በቅዱሳኑ ስም እንጠይቃለን፡፡
“ቡራኬያችሁና ጸሎታችሁ አይለየን”
የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ምእመናን ተወካዮች
ግልባጭ
 •  ብፁዕ አቡነ ናትናኤል አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ
 •  ለመንበረ ፓትሪያሪክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት
 •  ለፓትሪያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት
 •  ለምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት
 •  ለምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደርና ጸጥታ ዘርፍ ጽ/ቤት

_____________________________________________________________________________

የምሥራቅ ጎጃም ምእመናን በብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ በደል ማዘናቸውንና መማረራቸውን ገለጹ ክፍል (፩)

 •  ሊቀ ጳጳሱ ስድሰት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በ38 ሰዎች ላይ ሹም ሽርና እገዳ አካሄደዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ከወንድም ልጅ ጀምሮ እስከ ወዳጅና የሀገር ሰው የሚዘልቅ የዝምድናና የጎጠኝነት ትስስር ያላቸው መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡
 •   ብፁዕነታቸው በትዕቢትና በንቀት በብዙ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ የተናገሯቸው ንግግሮች ምእመናንን እጅግ አሳዝኖአል።
 •  የሀገረ ስበከቱ ካህናትን ውኃ ግድግዳ ላይ መርጨት ብቻ የለመዱ ወንጌል ያልገባቸው ሲሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶችንና ማኅበረ ቅዱሳንን ደግሞ “ወንበዴዎች፣ሌባዎች፣አሸባሪዎች” ብለው መሳደባቸውን የደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡
 •  “እኛ የምንሰብከው ዛሬ ጠፍቶ የተገኘውን መስቀል ሳይሆን መስቀሉ ላይ የተሰቀለውን ክርስቶስን ነው” አቡነ ማርቆስ በዘንድሮ የመስቀል በዓል ላይ የተናገሩ
 • ክፍል አንድ

(አንድ አድገን ኅዳር 29/2005 ዓ.ም ) ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በ1997 ዓ.ም ከ4 ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በቅዱስ ሲኖዶስ የጵጵስና ማዕረግ የተሰጣቸው አባት ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው ለ 17 ዓመታት ያህል በውጭ ሀገር የቆዩ ሲሆን ወደ ሀገር ቤት-ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ በመጀመሪያ ከ1997 ዓ.ም2001 ዓ.ም የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፤ ከ2001 ዓ.ም- 2003 ዓ.ም የአዊና መተክል ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ሆነው ከቆዩ በኋላ የጥቅምት 2004 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስን ስብሰባ ተከትሎ በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ተወልደው ባደጉበት፣ በተማሩበትና በቅኔ መምህርነት ባስተማሩበት የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው በማገልገል ይገኛሉ፡፡
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀጳጳስ ሲሆኑ ወደ ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት እንደመጡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በመልካም አቀባበል የተቀበላቸው ሲሆን በተለይም ከወጣቱ የቤተክርስቲያኒቱ ክፍል ጋር ውጭ ሀገር ለብዙ ዓመታት መቆየታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት የሰመረ አገልግሎት ይኖራቸዋል የሚል ግምት የነበረ ሲሆን ብፁዕነታቸውም ይህን ግምት  እውን የሚያደርጉ ብዙ እቅዶችና ሃሳቦች እንዳሏቸው በብዙ መድረኮች ቢሰነዝሩም ገና ሦስት ወራት ሳይቆዩ ብዙ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችንና ትውፊቶችን በቸልተኝነትና በድፍረት ማቃለል መጀመራቸውና በሀገረ ስብከቱ ላይ ቃለ አዋዲውንና ተዋረዱን ያልጠበቁ ፍትሐዊ ያልሆኑ መጠነ ሰፊ ሹም ሽሮችንና እገዳ ማካሄድ  መጀመራቸው ጉዟቸውን ከጅምሩ እንከን እንዲገጥመው አድርጎባቸዋል፡፡
በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እና በደብረማርቆስ ወረዳ ቤተክህነት ብቻ (በሀገረ ስብከቱ ያሉ 18 ወረዳ ቤተ ክህነቶችን ሳይጨምር) በ34 ሰዎች ላይ ሹም ሽርና እገዳ ያካሄዱ ሲሆን የብዙዎቹ በሥጋ ዝምድና፤ በቀድሞ ወዳጅነት፣ በጎጥና በአድር ባይነት የተደረገ ሲሆን የብዙዎቹ ሹም ሽርና እገዳም ሕገ ቤተክርስቲያንን ያልተከተለ በእርሳቸው ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆኑን የደብረ ማርቆስ ምእመናን ያቀረቡባቸው የሰነድ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ በዚህ አካሄዳቸው የተነሳም ለአንድ መንፈሳዊ አባት ሊሰጡ ቀርቶ ሊታሰቡ በፍጹም የማይገባቸውን በጽሑፍ ለመጻፍም የሚከብዱ የአፍሪካና ሌሎች ሀገሮች አምባገነን መሪዎች ስሞች እየተሰጧቸው መሆኑን የደረሰን መረጃ ይገልጻል፡፡
ብፁዕነታቸው በምእመኑ ዘንድ በጥብቅ የሚከበሩትንና ያልተለመዱትን የእምነቱም መጠበቂያ የሆኑትን ሃይማኖታዊ ጉዳዮችና ትውፊቶች በቸልተኝነት በድፍረት በተግባርና በንግግር መተላላፋቸው መፈጸማቸው ምእመናንን በእጅጉ ማሳዘናቸውን በተደጋጋሚ ለብጹዕነታቸው በምሬት መግለጣቸው ምንጮቻችን ገልጠዋል፡፡ ካህናት በንስሐ ልጆቻቸው ቤት በመሄድ የሚረጩትን ጠበል “ውኃ ” ካሉ በኋላ “ውኃ ግድግዳ ላይ ከመርጨት በቀር ወንጌል የማያውቁ” ብለው ካህናትን ሲሰድቧቸው ካህናቱም “ብዙ እናውቃለን ብንናገር ግን እናልቃለን” ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ ሊቀ ጳጳሱ በቤተክርስቲያኒቱ /ቅዱስ ሲኖዶስ/ እውቅናና ሕግ ወጥቶላቸው የተቋቋሙትን ሰ/ት/ቤቶችን በንግስ በዓል ላይ “ሌባዎች አሸባሪዎች” በማለት የሰ/ት/ቤት መለያ-ዩኒፎርም የለበሱትን በምእምኑ ፊት ሲያሸማቅቁ በሀገረ ስብከቱ ያሉ ሁሉንም ወረዳ ቤተ ክህነቶችን  ሰብስበው ማኅበረ ቅዱሳንን “ወንበዴዎች” በማለት መሳደባቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
በተጨማሪም እርሳቸው ወደ ሀገረ ስብከቱ ከመጡ ከአንድ ወር በኋላ ጀምሮ “እኔ ልማታዊ ነኝ ጊዜውን በአግባቡ መጠቀም አለብን”በሚል ተገቢ ባልሆነ ምክንያት የሃይማኖተ አበው መጽሐፍ እንዳይነበብ መከልከሉ፤ መቅድመ ተዓምረ ማርያምም መቅረቱና ካላንደር ነው ማለታቸው፤ የቅዳሴው ጸሎት እንደተፈጸመ የእርሳቸው የቅዳሴ ጠበሉን በጆግ በጅምላ ምእመናንን መርጨት መደጋገም፤ የታቦተሕጉን መንበር በመግለጥና መጋረጃውን በመክፈት ቤተመቅደሱን ቀና ብሎ ለማየት በሚሰቀጥጥ ሁኔታ እንዲቀደስ ማስገደድ፤ በልዩ ልዩ የወረዳ አድባራትና ገዳማት ላይ “መልክዓ መልክኡ ፤ማኅሌቱ፣ተዓምረ ማርያምም ቢሆንኮ ደብተራ የደረሰው ነው” እያሉ በምእመኑ ዘንድ በጥብቅ የሚከበሩትን ሃይማኖታዊ ጉዳዮችና የሃይማኖቱ በጎ ትውፊቶችና እሴቶችን ማቃለላቸውና እንዲተው ማስገደዳቸው በምእመኑ ዘንድ ከፍተኛ ሀዘንና ቁጣን ቀስቅሷል፤ ጉዳዩም ስህተት ሳይሆን መሠረታዊ የማንሸራተት ስትራቴጂ መሆኑን በተደጋጋሚ እየተገለጸ ይገኛል፡፡
 ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ለቅዱሳን ያላቸውን አመለካከት “ቅዱሳንን የቀደሰ ክርስቶስ ነው ስለሆነም ወንጌል ክርስቶስ ነው እንጂ መነኩሴ አይደለም፤ አቡሀይ እሙሀይ አትበሉ ክርስቶስን ስበኩ” በማለት በግልጽ በሕዝብ መሀል ተናግረዋል፡፡ በ2004 ዓ.ም ጾመ እግዚእ/ዐብይ ጾም/ ወቅት በደብረ ማርቆስ ጽርሐ ጽዮን አብማ ማርያም ቤተክርስቲያን በተደረገ ጉባኤ ላይ ከበሮ እያስመቱ ያስጨበጨቡ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ ለቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ያላቸው ዝቅተኛ ግምት እህቶቻችንና እናቶቻችን በወር አበባ ወቅት እንዲገቡ መፍቀዳቸውና ማስገደዳቸው፤ ጸሎተ ቅዳሴውን አቋርጦ መውጣት እንጂ መግባት እንደሚቻል በተደጋጋሚ መናገራቸው የብፁዕነታቸው አካሄድ አባታዊ ምክርና ማስተካከያ ሳይሆን መሠረታዊ የሃይማኖት ችግር መሆኑን ምእመናን እንደተረዱ ገልጸዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በዞኑ ዋና  ከተማ  ደብረማርቆስ ከሚገኙ 9 አድባራትና ገዳማት በስድስት ወራት የ8ቱን አስተዳዳሪዎች ለውጠዋቸዋል፡፡ከእነዚህም ውስጥ የ4ቱን ለ3ኛ ጊዜ ቀያይረዋቸዋል፡፡ የአንዱ ቤተክርስቲያንም ቢሆኑ ሊቀ ጳጳሱ ሲጠሯቸው አቤት ሲልኳቸው ወዴት የሚሉ አድር ባይ በመሆናቸው ብቻ በኃላፊነታወ መሰንበታቸው ይነገራል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ ምእመናንም ከብፁዕነታቸው ጋር ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የመንግሥት አካላትንም በመጨመር የሞከሩ ቢሆንም “እናንተ አታውቁኝ እኔ አላውቃችሁ” ቢሉም “አባታችን እርስዎ ባያውቁንም እኛ እናውቅዎታለን ያወያዩን”  ብለው ከከተማው “ከእናንተ ጋር እነጋገር ዘንድ አባትነቴም አይፈቅድልኝ ከፈለጋችሁ ጥያቄያችሁን ለሰበካ ጉባኤያችሁ አቅርቡ እንጂ ከማንም ውሪ-(ጉብል፣አላዋቂ ልጅ እንደማለት) ጋር ምን በወጣኝ፣ ማንም  ጳጳስ የማያደርገውን ያቀረብኳችሁም ስለገባኝ እንጂ የእኔ ድርሻ አይደለም” በማለት በአባትነታቸውና በቤተክርስቲያን እጂጉን አዝነው መመለሳቸውን የደረሰን መረጃ ይገልጻል፡፡
የዞኑ የመንግስት ከፍተኛ የአስተዳደር አካላትም ችግሩን ለመፍታት ከመጓጓት የተነሳ ከሚገባው በላይ በመንቀሳቀስ “ብፁዕነትዎ የልጆችዎን ጥያቄና አስተያየት ይስሟቸው” በማለት ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከነጋዴ ባለሀብቶችና ከሰ/ት/ቤቶች የተወከሉትን  እስከ ማወያየት የደረሰ ብርቱ ጥረት ቢያደርጉም እንዳልተሳካ የደረሰን መረጃ ያብራራል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ምእመናንንም  ቅዱስ ሲኖዶስ አስፈላጊውን መፍትሔ እንዲፈልግላቸው የቤተክርስቲያኒቱን አማኞችም በጸሎት እንዲያስቧቸው ጠይቀዋል፡፡
በቀጣይ በተለይ ብጹዕነታቸው በግብረ ሲሞን ስላከማቹት ሀብትና ስለፈጸሙት አስተዳደራዊ በደል እንዲሁም በሃይማኖታቸው ርቱዓን የሆኑ ምእመናን የያዙባቸውን የድምጽ ወምስልና የሰነድ ማሰረጃዎች የምናቀርብ መሆኑን እንገልጻለን!!!

ለጽሁፎች ሁሉ የድምጽ ፤ የምስል ፤ የሰነድ ማስረጃዎች በእጃችን ይገኛሉ
ቸር ወሬ ያሰማን!
የቅዱሳን አምላክ ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን
Advertisements

2 thoughts on “ዜናዎች

 1. mekuria

  እባካችሁ ከጎጃም ላይ ጥላሸታችሁን አንሱልን በቅዱሳን ላይ አትረማመዱ ደፋሮች

  Reply

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s