በጋሻው ደሳለኝ በይቅርታ ሚዛን ተመዘነ÷ ቀልሎም ተገኘ – ምእመኑን አስቆጣ አባቶችን አሳዘነ! የ‹ፀጉራሙ በግ› ታሪክ በሐዋሳ ተደገመ
- ‹‹በነበረው ሒደት በተለያየ ምክንያት ለበደላችኹን ኹሉ ይቅርታ አድርገንላችኋል፤ እናንተም ይቅርታ አድርጉ፤›› (በጋሻው ደሳለኝ፣ ኅዳር ፳፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.፤ ለሐዋሳ ደ/ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ምእመናን የተናገረው)
- ‹‹ይኼ ጉልበት ላይ መውደቅ፣ ይቅርታ መጠየቅ በፍጹም እንዳያደርገው፡፡ ጉልበት ላይ መውደቅ፣ ይቅርታ መጠየቅ ማለት ጥፋተኛ ነኝ፤ ተሸማቅቄ እኖራለኹኝ ማለት ነው፤›› (በጋሻው ደሳለኝ፣ ግንቦት ፳፻፬ ዓ.ም. የክብረ መንግሥት ግብረ አበሮቹን ሲመክር)
- የሐዋሳው የዕርቀ ሰላም መርሐ ግብር ከመጀመሩ አስቀድሞ በጋሻው ደሳለኝ የበደላትን ቤተ ክርስቲያንና ያሳዘነውን ምእመን ይቅርታ እንደሚጠይቅ በቤተ መቅደስ ለብፁዕ አቡነ ገብርኤል አረጋግጦላቸው ነበር፤ ብፁዕነታቸውም ሦስት ጊዜ ‹‹አጥፍቻለኹ÷ይቅርታ›› አሰኝተውት ነበር፡፡
- ይቅርታ ጠያቂ ሳይኾን ይቅርታ አድራጊ እና ይቅር ባይ መስሎ በቀረበው የበጋሻው ደሳለኝ የእብሪት አነጋገር ያዘኑት አቡነ ገብርኤል እና አቡነ ሉቃስ ምእመኑን ይቅርታ ጠይቀዋል፤ በጋሻው ከእንግዲህ በአህጉረ ስብከታቸው ስፍራ እንደማይኖረው በቁርጥ የተናገሩት አቡነ ገብርኤል፣ ‹‹እርሱ መቼም የሚስተካከልና የሚመለስ ሰው አይደለም›› ሲሉምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ‹‹አለመማር የሚያመጣው በሽታ ነው፤ ያሳዝናል›› ብለዋል፡፡